መልካም እሴቶች ይዳብሩ ተባለ
የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአጠቃላይ የኤጀንሲው ሠራተኞች ጋር የተሐድሶ /ዓመታዊ/ ክብረ በዓል አዘጋጀ፡፡
በዝግጅቱ በኤጀንሲው በተለያዩ ኃላፊነቶች ይሠሩ የነበሩት አቶ አብዲሣ መንገሻ፣ አቶ ቺንግ ራንግ፣ አቶ ፀጋዬ መብራህቱ እና አቶ አንዱዓለም ሙሻጎ የእውቅና ሽኝት ኘሮግራም ተካሂዶላቸዋል፡፡
የቀድሞ የባህርዳር ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲሣ መንገሻ ለ17 ዓመታት ኤጀንሲውን ማገልገላቸውንና በተደረገላቸው የሽኝት ኘሮግራም መደሠታቸውን አስታውቀዋል፡፡
አቶ አብዲሣ ሕይወታቸው ዛሬም ሆነ ወደፊት ከዚህ ተቋም ጋር የተያያዘ እንደሆነና ከሲስተሙ እንደማይወጡም ተናግረዋል፡፡
አቶ አብዲሣ በሠራተኛው የተሐድሶ ኘሮግራም ሽኝቱ መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገውና ይህ ከ1999 ዓ.ም. ነሐሴ ወር መጨረሻ ወዲህ ተካሂዶ አለማወቁንና ከ12 ዓመታት በኋላ እንደገና መከበሩ አስደስቶኛል ብለዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ኘሮግራሞች በሠራተኛው እና በኃላፊዎች መከከል መልካም ግንኙነት እንደሚፈጥሩና አዘጋጅ ኮሚቴውንም ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ኤጀንሲው በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ለውጦችን ማሣየቱንና ለውጥ ለሃገር፣ ለተቋም እንዲሁም ለሠራተኛ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው ጥሩና ማንነትን ሊያሣዩ የሚችሉ እሴቶች ቢቆጠሩና ቢሻሻሉ መልካም ነው ብለዋል፡፡
አቶ አብዲሣ ለውጥ ሲደረግ መልካም እሴቶች ሊጣሉ እንደማይገባ፣ ጥሩ እሴቶች ተይዘው ሊዳብሩ እንደሚገባና አላስፈላጊ ልማዶችን ደግሞ ማስወገድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ይህ ክብረ በዓል መዘጋጀቱም ወደ አንድነትና ወደ ነባሩ እሴት መመለስ በመሆኑ ሊበረታታ ይግባል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም አዳዲስ አሠራሮች እየተጨመሩ የተሻሉ ውጤቶችን የሚያስመዘግብ ተቋም ያስፈልገናል ሲሉ አሣስበዋል፡፡
ኘሮግራሙ በተለያዩ አዝናኝና ቁምነገር አዘል ጥያቄና መልስ ውድድር፣ የቡና ማፍላትና የኬክ ቆረሣ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል፡፡
የተሐድሶ ኘሮግራሙ በበላይ ኃላፊዎች ተነሣሽነት መካሄዱንም የዝግጅት ክፍሉ ሠምቷል፡፡