“ማገልገል ክብር ነው”
August 20, 2019ፊውቸርድ ዜና
ኤጀንሲው ገና ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ41 ዓመታት ደከመኝና ሠለቸኝ ሣይሉ በፍቅር ያገለገሉት ወ/ሮ ካሠች ገበየሁ ሠራተኛው ጥሩ የሥራ ተነሣሽነት ሊኖረው፣ ሊተሣሠብ፣ ሊፈላለግና የቀድሞውንም ፍቅር ሊመልስ ይገባል ሲሉ ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ኢመህመድ፣ ኢፋርሚኮር፣ ፋርሚድ እና መፈአኤ የተሠኙ በርካታ ስያሜዎች እንደነበሩትና በ1969ዓ.ም. ኢፋርሚኮር በሚለው ስያሜ እንደተቀጠሩ ወ/ሮ ካሠች ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ካሠች ሴት በመሆናቸው ደስተኛና የብዙ ፀጋ ባለቤት እንደሆኑ ገልጸው ሴቶች የመውለድና የማሳደግ፣ የቤት ውስጥና የውጪ ሥራ ኃላፊነትን ደምረው የሚያከናውኑ ጠንካራ ፍጥረቶች ናቸው ሲሉ ገልፀውልናል፡፡
ኤጀንሲውን የ‹‹እናት ጓዳ›› እንደሚሉትና ምክንያታቸውም ድርጅቱን በጣም እንደሚፈልጉት፣ እንደሚያስቡለት እና እንደሚያስብላቸው፤ በተጨማሪም የሠራተኛውም መቀራረብና መፈላለግ ከፍተኛ እንደነበር ወ/ሮ ካሠች አስታውቀዋል፡፡
ወ/ሮ ካሠች ሴቶች መማርና ራሣቸውን ማብቃት እንዳለባቸው፣ ሴት ልጅ ኃላፊነትን ለመወጣትም ሆነ ለጥንቃቄም ጎበዝ በመሆኗ እንደ መንግሥት አቅጣጫ ሃምሣ በመቶ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት ያስፈልጋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡