ሞዴል የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚዲያ አካላት የሐዋሣ ቅርንጫፍን ሕዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ጉብኝት ባካሄዱት ወቅት ሞዴል የማኀበረሰብ መድኃኒት ቤትን በዋናነት በጤና ሚኒስቴር ተጠናክሮ ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ናፍቆት ብርሃኑ ገለጹ፡፡
ኃላፊው የሞዴል የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ዋንኛ ዓላማ ለማኅበረሰቡ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀላሉ እንዲደርስ ማድረግ እንደሆነና የመድኃኒት ማዘዣ ይዞ ለሚመጣ ማንኛውም ተገልጋይ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ታካሚዎች መድኃኒት ታዞላቸው ለማግኘት ተቸግረው በፍለጋ እንዳይዳክሩ ከጤና ተቋማት አንድ ኪሎ ሜትር ባላነሰ ርቀት ላይ ተቋቁመው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ እንደሚገኝም ኃላፊው አክለዋል፡፡
የሞዴል መድኃኒት ቤቶቹ ዋና ተግባራቸው አቅርቦቱን ማሻሻል እንደሆነና ትርፍ ላይ ሳያተኩሩ የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ሣምንቱን ሙሉ የበዓል ቀናትን ጨምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጡ አቶ ናፍቆት አስረድተዋል፡፡
አቶ ናፍቆት ለረጅም ጊዜ ህመም የሚታዘዙ መድኃኒቶች ለምሳሌ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የልብ ህመም፣ የሚጥል በሽታና ከእንቅርት ጋር የተያያዙ ህመሞች መድኃኒቶችን በአካባቢው ያለውን የህመምተኞች መረጃ ያማከለ አቅርቦት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ለሚመጡ ተገልጋዮች ከመድኃኒት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ኪሎ፣ ቁመት፣ የቁመትና ክብደት ደረጃ (BMI-Body mass index) እንዲሁም የደም ግፊት የሚለኩ ዲጂታል ማሽኖችን በመጠቀም አገልግሎት እንደሚሰጥ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
አቶ ናፍቆት አክለውም ለሕጻናት የሚሰጡ ምግቦችን ወላጆች በየሱቁና በየሱፐር ማርኬት ከሚገዙ ይልቅ በጤና ባለሞያ ምክር ታግዘው እንዲገዙና እንዲጠቀሙ ማድረግ አንዱ የሞዴል መድኃኒት ቤቶቹ ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ሞዴል ፋርማሲዎቹ ሀዋሳ አዳሬ ሆስፒታል፣ ወራቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዲላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ሶዶ ሆስፒታል ላይ መቋቋማቸውን ኃላፊው ተናግረው በሌሎች ሆስፒታሎችና ተገልጋይ በሚበዛባቸው ነባር ጤና ተቋማት ላይ የማስጀመር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሞዴል መድኃኒት ቤቶቹ የሚፈልጉትን መነሻ መድኃኒት በማቅረብ ለዚህ ተግባር መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አቶ ናፍቆት አክለው ገልጸዋል፡፡