በኤጀንሲው የችግኝ ተከላ ተካሄደ፡፡
ኤጀንሲው ‹‹አረንጓዴ አሻራ እናሳርፍ፣ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኝ እንትከል!›› በሚል መሪ ቃል በመላው ሀገሪቱ የችግኝ ተከላ መካሄድን አስመልክቶ በዋ/መ/ቤት ሐምሌ 22 ቀን ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት ችግኝ ተከላ አካሄደ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም የችግኝ ተከላው ሀገራዊ ተልዕኮ ሲሆን ለኤጀንሲው ተልዕኮም አጋዥ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በሀገራችን እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች በሞቃታማና ቆላማ ቦታዎች እንደሚከሰቱና በአሁን ሠዓት ባለው የአየር መለዋወጥ ምክንያት ወባ ያልነበረባቸው አካባቢዎች በሽታው ሊከሰትባቸው ይችላል ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
የዕፅዋቱ መተከል በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት በድንገት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል አብዛኞቹ መድኃኒቶች የሚቀመሙት ከዕጽዋት በመሆኑ እጽዋቶችን መትከል ፈርጀ ብዙ ጥቅም አለው ሲሉ ዶ/ር ሎኮ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ችግኞቹ በግቢው ውስጥ መተከላቸው በቅርበት ሆኖ ለመንከባከብ እንደሚረዳና ጠቃሚነቱ የጎላ ነው ሲሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የችግኝ ተከላው በዚህ እንደማያበቃና እንደአስፈላጊነቱ ቀጣይነት ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አለምጸሐይ ዳታ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በሞጆ ከተማ የችግኝ ተከላ መካሄዱንና አሁን ለሦስተኛ ጊዜ በዋናው ግቢ እንደተከናወነ አስታውቀዋል፡፡
ኤጀንሲው በማኅበረሰብ ጤና ላይ የሚሠራ እንደመሆኑ ችግኝ ተከላው በቀጥታ ከጤና እንክብካቤ ጋር እንደሚገናኝና ዕፅዋት ከውበታቸው ባሻገር ከመጠን ያለፈ ሙቀትን በመከላከል ሠራተኛው ንጹሕ ዓየር እንዲያገኝና ጤንነቱ እንዲጠበቅ ይረዳል ሲሉ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ አለምጸሐይ አክለውም ወጣቶች እንደወጣትነታቸው የአባቶችን አደራ እንደተረከቡ ሁሉ ለመጪው ትውልድ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ታላቅ ሚና መጫወት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
አንዳንድ የኤጀንሲው ወጣት ሠራተኞች ዕፅዋቶቹ ከውበት ባሻገር በዓለም ላይ ያለውን የሙቀት መጠንና የዓየር ንብረት መዛባት ለማስቀረት ጉልህ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው የችግኝ ተከላው ሊበረታታ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹ አክለውም አባቶች ለእኛ ያስረከቡንን ንጹህና የተስተካከለ የዓየር ንብረት እኛም በተራችን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ አለብን የሚል ዓላማ ሰንቀው ችግኙን እንደተከሉ ገልጸዋል፡፡