“አቅራቢዎች መንግሥት ለዘርፉ ምርታማነት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙበት ይገባል” ዶ/ር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስተር

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
አራተኛው አለም አቀፍ የህክምና ግብዓት አቅራቢዎች ጉባኤ << ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ትብብር ለጋራ ራዕይ ማቀናጀት ጠንካራ አጋርነትን መገንባት >> በሚል መሪ ቃል የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፣ የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች ፣አለም አቀፍ አቅራቢዎች ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች ፣ የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች ፣ ዳይሬክተሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል ።
የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት በርካታ የተመቻቹ እድሎች በመኖራቸው ይህንን ተጠቅመው የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦትን ልዕልና ለማምጣት ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጥሪ አቅርበው ፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመድኃኒት አቅራቢዎች ውስን በመሆናቸው የአቅራቢዎች ቁጥር ለማሳደግ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለው ጥራቱን የጠበቀና ያልተቆራረጠ አቅርቦት ለአገልግሎቱ በማድረስ የጤናው ዘርፍ እንዲጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
መንግሥት መድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ምርትና አቅርቦት ላይ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እንደ ነርቭ፤ ካንሰርና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የአቅራቢዎች ውስንነት እንዳለ የገለጹት ሚኒስትሯ፥ አቅራቢዎች መንግሥት የፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የአገራችንን ብሎም የአህጉራችንን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ጉባኤው የሚካሄደው የህክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያለውን የግንኙነት አድማስ በማስፋት የሀገር ዉስጥ አቅራቢዎች አቅምን ለማሳደግ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ተናግረው ፤ የሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት አምራቾችን የምናበረታታበት ፣ በተደጋጋሚ እጥረት የሚነሳባቸው ውስን አቅራቢ ያላቸው መድኃኒቶች ላይ አቅራቢዎችን የምንስብበት እንዲሁም ከሁሉም በላይ አቅራቢዎች ወደ ሀገራችን መጥተው እንዲያመርቱ ለመጋበዝ ታልሞ የተዘጋጀ ኮንፍረንስ ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል ።
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ አምራችነትን ከጀመረች በርካታ አመታትን ብታስቆጥርም በህክምና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ተገቢውን ለውጥ እያሳየች አለመሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒትና የህክምና መገልገያ አምራቾች ኢንደስትሪ ማህበር ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶሌ ተናግረው ፤ አገልግሎቱ በአሁኑ ወቅት ለሀገር ውስጥ አምራቾች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ አቅራቢዎች እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።
በጉባኤው የሀገር ውስጥ መድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ አሁናዊ ሁኔታ ፣ የተሻሻሉ ጉዳዮች እና ተግዳሮቶች ፤ ሀገራዊ የጤና ፖሊሲው ምን እንደሚመስል ፣ የአገልግሎቱ ስትራቴጂካዊ እቅድና ማሳካት የሚሻቸው አንኳር ጉዳዮች ፣ በዘርፉ ያሉ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦች ላይ ዝርዝር ሪፖርት የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ አቅርበዋል ።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የህክምና ግብዓት አምራቾች ዘርፍ ለኢንቨስትመንት ያሉ ምቹ ሁኔታዎች ፣ የ2016 ዓ.ም በጀት አመት የአቅራቢዎች አፈፃፀም ፣ የህክምና ግብዓቶች ዙሪያ የሚደረገው ቁጥጥር ምን እንደሚመስል በዝርዝር ቀርቦ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ተነስቶ ውይይት ተካሂዷል ።
በጉባኤው ማጠቃለያ በ2016 ዓ.ም በህክምና ግብዓት አቅርቦት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ እና ልዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አለም አቀፍ አቅራቢዎች እና ሀገር አቀፍ አምራቾች የእውቅና ስነስርዓት ተካሂዷል ።
ማገልገል ክብር ነው!
ማኅሌት አበራ