ኤጀንሲው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችሉ የህክምና ግብዓቶችን እያሰራጨ መሆኑን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የህክምና ግብዓቶችን እያሰራጨ መሆኑን የኤጀንሲው የክምችትና ስርጭት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አድራሮ ሚያዝያ 06 ቀን 2012 ዓ.ም ገለጹ፡፡
ኤጀንሲው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችሉ 200 ሺ N 95 የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ሰርጅካል የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ 1 ሚሊየን የፊት መከላከያ ፕላስቲክ፣ 21 ሚሊዮን ጓንት፣ አልጋ፣ የሙቀት መጠን መለኪያ ቴርሞ ሜትር ለጤና ባለሞያዎች የሚሆኑ ልብሶችና ሌሎች መከላከያዎች በአጠቃላይ 13 የሚሆኑ የፊትና የሰውነት መከላከያ ግብዓቶች (Personal Protective Equipments) መሰራጨታቸውን አቶ ተስፋለም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ህክምናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ኦክስጂን ኮንሴንትሬተር ፣ ኦክስጅን ሲሊንደር፣ ሜካኒካል ቬንትሌተር እና ሌሎች የህክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶችን ጭምር መሰራጨቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ስርጭቱ የተካሄደው ለለይቶ ማቆያ እና ህክምናውን ለሚሰጡ በፌዴራልና በክልል ለተለዩ ሆስፒታሎችና ተቋማት በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትውት የስርጭት ክፍፍል መሰረት መኆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ኢንስቲትዩት በአስቸኳይ እንዲገዙ የተጠየቁ 700 ሺ ሊትር ሳንታይዘር ለሁሉም ክልሎች እየተሰራጨ ሲሆን 200 ሺ ሊትር አልኮል፣100 ,ሺ N 95 ፌስ ማስክ፣ 14 ሚሊዮን ሰርጂካል ፌስ ማስክ እና ሌሎች የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ በቅርቡ የሚገቡ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ኤጀንሲው ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ግምታዊ ዋጋቸው ከ200 ሚሊዬን ዶላር ወጭ ሊኖራቸው የሚችሉ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ግብዓቶች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች እና የህክምና መገልገያዎችን ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ገዝቶ ለማቅረብ የግዥ ሂደታቸው መጀመሩ ተገልጸዋል፡፡