ከ12ሺ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዙሪያ ከጤና ተቋማት ጋር የተደረገ የዌቢነር ውይይት በስኬት ተጠናቋል፡፡
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት መሻሻል ውጤታማነት ዙሪያ መጋቢት 3/2017ዓ.ም ዌቢናር በበይነ መረብ ያከናወነ ሲሆን ፤ ዌቢናሩ በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፣ በጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ እና በአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ የተመራ ሲሆን ፤ የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ፣ የአገልግሎቱ 19ኙ ቅርንጫፎች ፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ፣ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎች ፣ የወረዳ ጤና ቢሮዎች ፣ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች በአጠቃላይ ከ12ሺ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ዉይይት ተከናዉኗል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዌቢናሩ መክፈቻ ንግግር እንዳሉት አዲሱን አዋጅ መሰረት አድርጎ የወጡ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች የአተገባበር ሁኔታ ፣ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተሰሩ ስራዎችን በጥልቀት ለመመልከት ፤ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም ለማሳደግ ፣ በህክምና ግብዓት ዙሪያ ያሉ ቁጥጥር ስርዓቱን ለማሻሻል ፣ የቀጥታ ስርጭት አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት በመዘርጋት የመረጃ ግልፀኝነትን መፍጠር በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ውጤታማ የሆነ ውይይት እንደሚካሄድ ዕምነታቸውን ገልፀዋል ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ አዳዲስ ጉዳዮች ፣ የታዩ መሻሻሎችና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ፤ የአቅርቦት ሰንሰለት ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓት ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ዙሪያ ፣ በህክምና ግብዓት የክምችት እና የስርጭት ሁኔታ መሻሻል ፣የሀገር ውስጥ አምራቾች አቅምን ማሳደግ መቻሉ ፣ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለጤናው ዘርፍ የሚሰጠው ዕድል በአቅርቦት ሰንሰለቱ ዙሪያ የተከናወነው ጠንካራ ስራዎችን በዝርዝር ዶ/ር አብዱልቃድር አቅርበዋል ።
በአይነቱ ልዩ የሆነው የዌብነር ውይይት በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ቁልፍ ከሆኑት ጤና ተቋማት ጋር ወጥ የሆነ መረጃ ከሁሉም ጋር በተመሳሳይ እንዲሰራጭ በማድረግ ፤ ጊዜ ፤ጉልበትን እና ሀብትን በመቆጠብ መወያየታችን በሁላችንም ዘንድ ችግሮችን በመፈታት ለህብረተሰባችን መድኃኒት ሳይቆራረጥ ለማቅረብ ያለንን ቁርጠኝነት እና ተነሻሽነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡በውይይቱ የተሳተፍ፤እንዲሳካም ለተባበሩ ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና ይደረሣችሁ ሲሉ ዶ/ር አብዱልቃድር ገልጸዋል፡፡
በዌቢናሩ ላይ የዲጂታላይዜሽን ስርዓት መዘርጋት እስከ ጤና ተቋማት በማውረድ የመረጃ ግልፅኝነት መፍጠር ፣ በጤና ተቋማት በኩል ያለው የህክምና መሳሪያ አጠቃቀምን ማሻሻል ፣ የሀገር አቀፍ የህክምና ግብዐቶች ዝርዝር ውስጥ ያልገቡ መድኃኒቶች የሚፈታበትን መንገድ ፣ የጤና ተቋማት ለትንበያ የሚሰጡትን ትኩረት እንዲያድግ ከመስራት አንፃር ፣ ወደ ፊት RDF መድኃኒቶች አቅርቦት ምን እንደሚመስል ፣ ዘርፉን በሰው ሀይል የተሟላ ከማድረግ አንፃር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እነዚህና መሰል ጉዳዮች ሰፊ ውይይት እንዲሁም በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል ፡፡
በቀጣይ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያሉ ተግዳሮቶች በጋራ በመፍታ የህክምና ግብዓቶች በክምችት የመገኘት ምጣኔን በማሳደግ የህብረተሰቡን እና የህክምና ባለሙያዉን እርካታ የምናሳድግበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለዉ ሲሉ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ጠቁመው ፤ ለዚህም በርካታ ችግሮችን የሚፈታው አዋጅ በመፅደቁ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ማስፈፀም የምንገባበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ማገልገል ክብር ነው !
