ከ5 ሚሊየን ዶዝ በላይ የኮቪድ-19 የክትባት መድኃኒቶች መሰራጨታቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከ5 ሚሊየን ዶዝ በላይ የኮቪድ-19 የክትባት መድኃኒቶችን ማሰራጨቱን የመጋዘን አያያዝ ክምችት አስተዳዳር ባለሙያ ወ/ሮ ማስተዋል አበባው ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም አስታወቁ፡፡የተሰራጩት የክትባት መድኃኒቶችም አስትራ ዜኒካ፣ሳይኖፋርም፣ጆንሰን ኤንደ ጆንሰን እና ፋይዘር ሲሆኑ በአጠቃላይ 5 ሚሊየን 60ሺህ 616 ዶዝ መጠን እንዳላቸው እና የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ ለሚካሄደው የኮቪድ-19 የክትባት ዘመቻ መሆኑን ወ/ሮ ማስተዋል አብራርተዋል፡፡ስርጭቱም በአዲስ አበባ ቁጥር 1 እና 2 ፣ በአርባ ምንጭ፣ በአሶሳ፣ በባህርዳር፣ በድሬደዋ፣ በጋምቤላ፣ በሐዋሳ፣ በጅጅጋ፣ በጅማና በነጌሌ ቦረና ቅርንጫፎች አማካኝነት ተካሄዷል ተብሏል፡፡ የክትባት መድኃኒቶቹም ለኦሮሚያ፣ለሲዳማ፣ለቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ለደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች፣ ለጋምቤላ፣ለሀረሪና ለሶማሌ ክልሎች፣ለድሬደዋ እና ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳዳር እንደተላኩ የተገለጸ ሲሆን 1 ቢሊየን 756 ሚሊየን 127 ሺህ 471 ብር የሚገመት ዋጋ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡እንዲሁም ክትባቱን ለመስጠት የሚያገለግሉ 7 ሚሊየን 469 ሺህ 267 ዋጋ ያላቸው ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች መሰራጨቱን ባለሙያዋ አክለዋል፡፡ የኮቪድ-19 በሽታ ወደ ሀገራችን ከገባ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት 368 ሺ 979 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን 6ሺ 630 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ህይወታቸው ማለፉ ጤና ሚንስቴር በዚህ ሳምንት መግለፁ ታውቋል፡፡የበሽታውንም ስርጭት ለመግታት እስካሁን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ክትባት ለህብረተሰቡ መሰጠቱና በተጨማሪም ከ8 ሚሊዮን በላይ ክትባት (ዶዝ) በእጅ የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ተጨማሪ ክትባቶች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ በመሆኑ በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ዜጎችን በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ ለተያዘው ዕቅድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየድርሻውን እንዲወጣ ሲሉ የኢፊድሪ ጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል ፡፡ሂ
ሩት ኃይሉ