ኮሌራን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት ተሰራጨ

በአፍ የሚሰጥ የኮሌራ ወረርሺኝ መከላከያ በኤጀንሲው በኩል ከሰኔ 11 ቀን ጀምሮ ለአፋር፣ ለኦሮሚያና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮች ስር ላሉ ጤና ተቋማት መሰራጨቱ ተነገረ፡፡
የመደበኛ ፕሮግራም መደኃኒትና የህክምና መገልገያዎች ክምችት አስተዳደር ባለሙያ አቶ አገኘሁ ናደው በአዲስ አበባ የተሰራጨው በአፍ የሚሰጥ የኮሌራ ክትባት መጠኑ 18 ሺህ 300 መቶ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡
ክትባቱ የተሰራጨባቸው በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለአራዳ፣ ቦሌ፣ ኮልፌ፣ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ጉለሌ፣ ቂርቆስ ልደታ እና የካ ክፍለ ከተሞች መሆናቸውን አቶ አገኘሁ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የቂልንጦ እና ቃሊቲ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ክትባቱ መሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተሰራጨው ክትባት አጠቃላይ ዋጋ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ አቶ አገ ኘ ሁ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ላሉ ወረዳዎች 29 ሺህ መጠን ያላቸው የኮሌራ ክትባት ከሰኔ 20 ቀን ጀምሮ እንደተሰራጩ ተናግረው ክትባቱ አጠቃላይ ወጪው 15.7 ሚሊየን ብር መፍጀቱን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በአፋር ከልል አሚባራ ወረዳ 6 ሺህ 100 የኮሌራ ክትባት መጠን የተሠራጨ መሆኑን አስታውቀው ለክትባቱ 3.3 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አቶ አገኘሁ ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ በተጠቀሱት ቦታዎች የክትባት ስርጭቱን ለማካሄድ 20 ሚሊየን ብር አካባቢ ወጪ መደረጉን ባለሙያው አክለው ገልጸዋል፡፡
ክትባቱ ሊከሰት የሚችል አዲስ የኮሌራ ወረርሺኝን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያግዝ ታስቦ መሰራጨቱን አቶ አገኘሁ በቆይታቸው ተናግረው ክትባቱን መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
የክትባት ሥርጭት የተካሔደው በጤና ጥበቃና በኢትዮጵያ ጤና ሕብረተሰብ ኢንስቲትዩት በተገኘው አቅጣጫ መሠረት መሆኑን ነግረውናል፡፡
ቀደም ሲል የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል ኤጀንሲው በቂ የመድኃኒት ክምችት እንዳለው እና ግብዓቶችን ሲያሰራጭ እንደነበረ እንዲሁም መድኃኒቶቹ በሀገር ውስጥ አምራቾችም ጭምር የሚመረቱ በመሆናቸው የክምችት መጉደል ስጋት እንደማያጋጥም መነገሩ ይታወሳል፡፡