የመድኃኒት፣ ህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎች የ6 ወር ዕቅድ
አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ
===============================
በጤና ሚኒስቴር የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎች መሪ ስራ አስፈጻሚ ከክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ ጋር በመቀናጀት ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌዴራል ሆስፒታሎች እና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ግምገማ በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡
የግምገማ መድረኩን በይፋ የከፈቱት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ፣ ባለፉት ዓመታት እንደሃገር የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎችንና መገልገያዎችን አቅርቦት ለማሻሻል ጥረት መደረጉንና በዚህም አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸው አሁንም በቀጣይ አቅርቦቱን ለማሻሻል ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ አክለውም እንደሃገር የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎችንና መገልገያዎችን አቅርቦት ለማሻሻል የተለያዩ ሪፎርሞች ተግባራዊ መደረጋቸው የጤና አገልግሎቱ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ቢሆንም ከጤና ተቋማት የሚቀርበው የፍላጎት ትንበያ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ በግምገማው ክልሎች ያላቸውን ልምድ በማካፈል ችግሮችን ማስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
የክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ የፕሮግራም ማናጀር አቶ ተስፋዬ ሰይፉ በበኩላቸው፣ ላለፉት 18 ዓመታት ድርጅታቸው የጤናውን ዘርፍ ስርዓት ለማገዝ የመድሃኒት አቅርቦትን በተለይም የኦክስጅን አክርቦትን ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ እንደነበር ተናግረው፣ በቀጣይም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከክልሎች ጋር ተባብሮ ለመስራትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ የአገልግሎቱን የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ሲያቀርቡ፣ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት 77 በመቶ የሚሆኑ ለጤና ፕሮግራም አገልግሎት የሚውሉ መድሃኒቶች የተሰራጩ መሆኑና 23 በመቶዎቹ ደግሞ በተገላባጭ ፈንድ መደበኛ በጀት (አር.ዲ.ኤፍ) ተገዝተው መሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አብዱልቃድር በሪፖርታቸው ጨምረው እንደገለጹት ወቅታዊ የጸጥታ ችግር፣ የመረጃና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የትንበያ ችግር ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰው በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የመድሃኒት፣ ህክምና መሳሪያዎችና መገልገያዎች መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ረጋሳ ባይሳ የግምገማ መድረኩ ለቀጣይ ሁለት ቀናት የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀው ሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌዴራል ሆስፒታሎችና ኤጀንሲዎች የ2016 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸማቸውን እንደሚያቀርቡ፣ የቀጣይ ስድስት ወራት ዕቅድ ላይም የማናበብ ስራ እንደሚሰራና የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳዳሮች፣ ኤጀንሲዎች፣ የፌዴራል ሆስፒታሎችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በመርሃ ግብሩ መሰረት ክልሎች የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡
