የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኤጀንሲው የስልጠናና ማማከር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኤኮኖሚክስ የፋይናንስና አካውንቲንግ የትምህርት ክፍል ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችንና የማማከር አገልግሎት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ምንተስኖት አድነው የትምህርት ክፍሉ ባልደረባ ገለጹ፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ዓለማቀፋዊ የሆነ የሪፖርት ስታንዳርድ IFRS /International finance reporting standard/ በኤጀንሲው እንዲተገበር ዩኒቨርሲቲው የትምህርትና የምርምር ተቋም በመሆኑ በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በኩል የIFRS አማካሪዎችና ኤክስፐርቶች እንዲሁም በኤጀንሲው በኩል የትግበራ ቡድን ተቋቁሞ የኤጀንሲውን የሒሣብ ሪፖርት በስታንዳርዱ መሠረት እስከ ህዳር 30/2019 ድረስ ሪፖርት ለማውጣት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
IFRS የሪፖርት ስታንዳርድ ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም መባቻ ጀምሮ የተዘጋጀ ሲሆን በሀገራችንም የኢትዮጵያ የአካውንቲንግና ኦዲት ሥራ ቦርድ ተቋቁሞ አስገዳጅ የሆነ ወጥ የፋይናንስ ሪፖርት ሥርዓት እንዲከተሉ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዓላማው ለተጠቃሚዎች የፋይናንስ ሪፖርቶችን ወጥ በሆነ ቅርጽና ይዘት በዓመት አንድ ጊዜ ሪፖረት ማውጣት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡
የአካውንቲንግ መረጃዎች በሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ ውሳኔዎች ትልቅ ግብዓት የሆነ የመረጃ ምንጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እንዲሁም የመንግሥት ባንኮች ኢንሹራንስና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ አነስተኛና መካከለኛ ማይክሮ ፋይናንሶች፣ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ የሪፖርት ስታንዳርድ እንዲተገብሩ በፓርላማና ፌደሬሽን ምክር ቤት የወጣ ያስገድዳጅ ህግ አለ ብለዋል፡፡
Supply chain of compassion!!!!!