ለኢ.አር.ፒ ፕሮጀክት አሰልጣኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
አገልግሎቱ አሰራሩን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተቀናጀ መረጃ ስርአት (ERP) ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የሲስተም ፍተሻዉ ተጠናቆ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚጀምርበት (Go Live) ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በዚህም ከዋናዉ መ/ቤት እና ከቅርንጫፍ ለተወጣጡ አስቀድመዉ የTOT ስልጠና ለወሰዱ አሰልጣኞች እንዲሁም ለኢ.አር.ፒ ፕሮጀክት አሰልጣኞች ባሣለፍነው ሣምንት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናዉ የኢ.አር.ፒ ፕሮጀክት ቴክኒካል አማካሪ አቶ ጀማል ዳዉድ እና በጤና ሚኒስቴር የሰዉ ሃብት ማሻሻያ ሙያዊ አማካሪ አቶ ለታ ይታገሱ ዉጤታማ አሰልጣኝ ለመሆን የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን፤ በስልጠናዉ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በምን መልኩ መፍታት እንደሚችሉ እና ምን አይነት ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ እንደሚገባቸዉ ለሰልጣኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፅሑፍ አቅርበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም በይፋ የሚጀምር ሲሆን፤ ከመጋቢት 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 6 ሳምንታት በተለያዩ ሞጁሎች ላይ ከሁሉም ቅርንጫፎች ለተውጣጡ 700 ሰራተኞች በዋናዉ መ/ቤት፤ አዳማ እና ሀዋሳ ቅርንጫፎች ላይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ የፕሮጀክቱ ማናጀር ወ/ሮ መንፈሴ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
አክለዉም ቆጠራን በጊዜ በማከናወን፤ ወደብ ላይ ያሉ ግብአቶችን ቶሎ ተቀብሎ ወደ ቅርንጫፍ በማሰራጨት ለጤና ተቋማት ተደራሽ ማድረግ፤ ቅርንጫፎች ከፕሮጀክት ቢሮ የሚጠየቁ መረጃዎችን በተቀመጠዉ የጥራት መለኪያ መሰረት በፍጥነት በመላክ፤ ጤና ተቋማት የሚያስፈልጋቸዉን ግብአቶች ቀድመዉ በመዉሰድ እንዲሁም ሰራተኞች ለስልጠናዉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በንቃት በመሳተፍ ለፕሮጀክቱ መሳካት ሁሉም ድርሻዉን እንዲወጣ ወ/ሮ መንፈሴ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
#ማገልገል ክብር ነዉ
ሰላም ይደግ
