በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ የአቅርቦት ሰንሰለቱ አመራሮች ሰነድ ላይ ሲደረግ የነበረው ውይይት
በአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ለ3 ቀናት ሲካሄድ የነበረዉ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ዝቅተኛ የአገልግሎቱ አመራሮች በሚታዩ የክህሎት፣ የስነ ምግባር እና የአመለካካት ተግዳሮች ተቋማዊ ሠነድ ተዘጋጅቶ ችግሮቹ በጥልቀት ተዳሰዋል።
የዉይይት መድረኩ ችግሮችን ውጫዊ ሳይደረጉ ሁሉም አመራር የየድርሻውን በመውሰድ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ተጠናቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በንግግራቸዉ የአገልግሎቱን ስራዎች በቅርበት እንደሚከታተሉ ገልፀው የህዝቡን የህክምና ግብዓቶች አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና አሁን በየደረጃው ያለው የአቅርቦት ሰንሰለት አመራር መመለስ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
አገልግሎቱ ለሚሠራቸው ማንኛውም ስራ የሚንስቴር መ/ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው በአህጉር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ እና ዘመናዊ አሰራርን (Digitization) በመተግበር የፈጠራ ስራዎችን በማከል ትጉ የለዉጥ አመራር ሊኖር እንደሚገባ አንስተዋል።
በተያያዘም የስራ ባህላችንን በማዳበር የተጀመረዉን የለዉጥ ምዕራፍ እስከ ታች በማዉረድ የህክምና ግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል እንደሚገባ ሚኒስቴሯ ጠቁመዋል ።
ዉል የተገባለት አቅርቦት ስርአቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት የጤና ሚኒስቴር ዲኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ፤ ተቋሙ ባስመዘገባቸዉ ስኬቶች መዘናጋት እንደሌለበትና ጥራት ያለዉ የአገልግሎት አሰጣጥን ማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ እንዳሉት የስራ ባህላችን ዉጤት ተኮር እንዲሆን ሁላችንም የተቋሙ አመራሮች በትብብር መንፈስ ህብረተሰባችንን ማገልገል ይጠበቅብናል፤ የአዳዲስ አመራሮችን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ አለብን ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የተቋሙ አመራሮችም በሰነዱ እና በውይይት ወቅት የተነሱ ችግሮችን ፈጥኖ በማረም የህዝብ አገልጋይነታችን ዳግም በማደስ በአፍሪካ ፈጣን ምላሽ ሰጭና ውጤታማ ሆነ ተቋምን በመገንባቱ ሂደት የበኩላቸዉን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል ።
#ማገልገል ክብር ነዉ
