በሐዋሳ ከተማ የተገነባው ዘመናዊ የመድኃኒት ማስወገጃ ኢንሲኔሬተር የሙከራ ሥራ መሥራት መጀመሩ ተገለጸ

በሐዋሳ ከተማ የተገነባው ዘመናዊ የመድኃኒት ማስወገጃ ኢንሲኔሬተር የሙከራ ሥራ መሥራት እንደ ጀመረ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሠ ዛሬ ሚያዝያ 25 ቀን 2011ዓ.ም. በፌስ ቡክ ገጻቸው አስነበቡ፡፡
ቀደም ሲል ግንባታው ተጀምሮ የነበረው የሐዋሳው ቅርንጫፍ ዘመናዊ የመድኃኒት ማስወገጃ ኢንሲኒሬተር በታቀደለት የጊዜ ገደብ መሠረት ግንባታውና የማሽነሪዎች ተከላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ከሚያዝያ 22/2011 ጀምሮ የሙከራ ስራ ጀምሯል ብለዋል፡፡
የኢንግሊዝ ሐገር የ 2018 ስሪት የሆነው ዘመናዊ የመድኃኒት ማስወገጃ ኢንሲኒሬተር ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን የህብረተሰቡን ጤናና አከባቢን በማይጎዳ መልኩ የሚያስወግድበት የመጨረሻው ቴክኖሎጂ (Latest technology) መሆኑን አቶ ዘመን ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂው እጅግ በጣም ዘመናዊ በመሆኑ ማሽኑን የሰራው ካምፓኒ /INCINCO/ በኢንግሊዝ ሐገር ሆኖ ኢንሲኔሬተሩን ማሰራት የሚችል ቢሆንም ስራው በባለቤትነት መሰራት የሚገባው በሀገራችን ባለሙያዎች በመሆኑ ለዚህ ስራ የተቀጠሩ የኤጀንሲያችን ባለሙያዎች /Mechanical Engineers/ የተግባር ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዘመን ኢንሲኔሬተሩ 99.99 % ከአከባቢ ብክለት የፀዳ /Environmental friendly/ እንዲሁም Ash content 3 % የሆነ ነው ሲሉ በተጨማሪ ገልጸዋል፡፡
ለኤጀንሲያችን ባለሙያዎች የሚሠጠው የተግባር ስልጠናና የክህሎት ሽግግሩ እንደተጠናቀቀ ኢንሲኔሬተሩ በአንድ ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሥራ የሚጀምር ይሆናል ሲሉም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡