በመድኃኒት ስርጭት ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ተሰጠ


የአዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ
የኢጣሊያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመድኃኒት ስርጭት ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎች የአዳማ ቅርንጫፍ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጡ፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በመድኃኒት አቅርቦቱ መዋቅራዊ ሠንሠለት ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎች የቅርንጫፉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ንጉሴ ከ19 ቅርንጫፎች ወደ ጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች መቶ በመቶ እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው በአሁን ሰዓት የቀጥታ ስርጭት ማድረግ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው በአፈጻጸም ደረጃ 70 በመቶ የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች የቀጥታ ስርጭት ተጠቃሚ መሆናቸውን ቀሪዎችን ደግሞ በወረዳቸው እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከክትባት ስርጭት ፈተናዎች ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄ አቶ ሰለሞን የመሠረተ ልማት ማሟያ ገንዘብ ችግር በዋነኝነት መኖሩን ተናግረው የክትባቶች ልዩ ባህሪ ሌላው ፈታኝ ነገር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በየትኛውም ቦታ የመረጃ ጥራት ችግር አለ ያሉት ኃላፊው በተለይ በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የመድኃኒት ፍላጎት መረጃ ችግር እንዳለ አስታውቀዋል፡፡
በሪፖርት በመጠየቂያ ቅፅ (RRF) መቶ በመቶ መረጃ ማግኘት እንደተቻለ ኃላፊው ተናግረው ጥራት ያለው መረጃ ከ50 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ኦቦ በበኩላቸው ጥራት ያለው መረጃ ለማግኘት የኤም-ብራና ሞባይል መተግበሪያ፣ ቴሌግራም እንዲሁም ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በምክክር ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሰለሞን ከሪቨርስ ሎጅስቲክ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ ዘመናዊ ኢንሲኔሬተር መተከሉን ተናግረው ከአካባቢው ጋር ተስማሚ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ በያዝነው ዓመት መጨረሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ1 ሺህ ጤና ጣቢያዎች በቀጥታ የክትባት መድኃኒቶችን ለማዳረስ ዕቅድ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
አክለውም መ/ቤታቸው በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ለጤና ጣቢያዎች የክትባት መድኃኒቶችን የማዳረስ ዕቅድ እንዳለው አስረድተው ዕቅዱን ለማሳካት የዋና መ/ቤት እገዛ ያስፈልጋል ሲሉ በአዳማ በተዘጋጀው መድረክ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዘጋጆች፡- ራሔል ታመነ፣ በፀሎት የማነና ማርቆስ ሙሉጌታ