በመድኃኒት ግዥ መዘርዝር ክለሳ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር አውደ ጥናት አካሄደ
የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በቀጣይ ሁለት አመታት ለሚያቀርባቸው የመድሀኒት ግዥ መዘርዝ /pharmaceuticals procurement list /ከባለድርሻ አካላት ጋር አውደ ጥናት ከነሀሴ 25-27/2012 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የመድኃኒት ግዥ መዘርዝሩ በየሁለት አመቱ የሚከለስ እንደሆነ እና በሂደት ላይ ያለውን መዘርዝር በጥልቀት በማየት፣ ከመዘርዝሩ ውስጥ የሚካተቱ፣ የሚወጡ፣በብዛት ተላላፊ ለሆኑ እና ላልሆኑ በሽታዎች የሚሆኑ፣አዋጭ ዋጋ ያላቸውን እና የጋራ መለያ በማስቀመጥ በመዘርዝሩ ለማካተት ታስቦ የተዘጋጀ ውይይት መሆኑን የኤጀንሲው የመድኃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች ግዥ አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ጊጋር በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
የህክምና ግብአቶችን ወደ መድኃኒት ግዥ መዘርዝር ስናስገባም ሆነ ስናስወጣ ግልፅ የሆኑ መስፈርቶችን ተጠቅመን ነው ሲሉ አቶ ጎይቶም ተናግረዋል።
በቀድሞ የመድሃኒት መዘርዝራችን የሌሉ ነገር ግን በተደጋጋሚ በጤና ተቋማት የሚጠየቁ፣የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አዳዲስ ፕሮግራሞች ማለትም ኩላሊት ንቅለ ተከላ አና ልብ ህክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች በአዲሱ መዘርዝራችን ትኩረት ተደርጎባቸዋል ሲሉ አብራርተዋል።
በመርፌ ሆነ በኪኒን መልክ በግዥ የምናቀርባቸው መድሀኒቶች ግራማቸውም ጭምር ተለይቶ አዋጭና ተመራጭ የሆኑት ብቻ በመዘርዝሩ ይካተታሉ በማለት አክለዋል።
መዘርዝሩ ሲዘጋጅ ታሳቢ ያደረገው ከአሁን በፊት በስራ ላይ የነበረውን ጨምሮ የመደበኛ መድሀኒት ግዥ መጠየቂያ ፍርም፣ የጤና ሚኒስቴር ወቅታዊ ፕሮግራም፣ በምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተመዘገቡ ምርቶች፣ሀገራዊ መሠረታዊ መድሀኒቶች መዘርዝር፣የአለም ጤና ድርጅት ዶክሜንቶችና መሠረታዊ መድሀኒቶች ዝርዝር፣ የህክምና ፖሊሲ እንዲሁም የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን ያገናዘበ ነው።
በአውደ ጥናቱ ላይ ከአዲስ አበባ እና ከክልሎች የተመረጡ የመንግስት ሆስፒታሎች አና ጤና ጣቢያዎች በካንሠር፣ በልብ፣ በጥርስ፣ በማህፀን፣ አናቶች፣ህፃናት በሌሎችም የህክምና ዘርፎች ስፔሻላይዝድ ያደረጉ እና የፋርማሲ ባለሙያዎች እየተሳተፍ ይገኛል።
ኤጀንሲው ከአሁን በፊት 1373 አይነት መድሀኒቶች፣የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች፣ የህክምና መገልገያ፣ ኬሚካል አና ሪኤጀንቶች ወስጥ 489 lመቀነስ እንዲሁም 140 አዳዲስ በመጨመር 1024 አይነት ልዩ ልዩ የህክምና ግብአቶችን በቀጣይ ሁለት አመታት ለማቅረብ ያዘጋጀውን ፕሮፖዛል ለውይይት አቅርቧል።
አወል ሀሠን