በአዲስ አበባ ከተማ የመድኃኒት አቅርቦቱን 95% ማድረስ ተችሏል
ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም አድራሮ Quick win initiative የተባለው አሰራር በአዲስ አበባ ውስጥ በተመረጡ 12 ሆስፒታሎች ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦትን ከ60 ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ እንዳስቻለ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም ለኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በጤና ጥበቃ አነሳሽነት የጀመረው የመድኃኒት አቅርቦቱን እጥረት ለማቃለል የታሰበው መንገድ መድኃኒቶችን ከማዕከል እስከ ታች ድረስ የሪፖርት ቅብብሎሽ በማሳለጥ መድኃኒቶች ለጤና ተቋማት በፍጥነትና በበቂ መጠን እንዲቀርቡ ያስችላል፡፡
ከግንቦት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እየተሠራበት ያለውን ይህን አሰራር በያዝነው በጀት አመት በ100 ቀን ዕቅድ ለ60 ሆስፒታሎች ለማስጀመር ታቅዶ በ48 ሆስፒታሎች እየተተገበረ እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው አጠቃላይ ሰልጥነው ስራ ለመጀመር ዝግጁ የሆኑ ሆስፒታሎች ቁጥር 76 መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ በ100 ቀን እቅዱ ማገባደጃ ላይ በ76ቱም ሆስፒታሎች እንደሚተገበር አክለው ገልፀዋል፡፡
አሰራሩ ሲጀመር ብዙ የጤና ተቋማት ምንም ለውጥ አያመጣም የሚል አመለካከት የነበራቸው ቢሆንም ጥቅሙን ሲረዱ ለውጤታማነቱ ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል ሲሉ ም/ዋ/ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ አሰራር ቀደም ሲል ከመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ኤጀንሲውን በሙስና የሚጠረጥሩና የሚወነጅሉ አካላት የነበራቸው ግምት ትክክል እንዳልነበርና የአቅርቦት ችግሩ ዋነኛ መንስዔ የተሳለጠ የመረጃ ቅብብሎሽ ባለመኖሩ እንደነበር የሚያሳይ ነው ብለዋል ም/ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
አክለውም የመድኃኒት አቅርቦት ችግር የኤጀንሲው ክፍተት ብቻ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ በአንድ በኩል የኮሙኒኬሽን ቅብብሉ ሙሉ በሙሉ በአግባቡ እየሄደ አልነበረም በሌላ በኩል ደግሞ የመድኃኒት አቅርቦት ሥራውን የኤጀንሲው ብቻ አድርጎ የማየት ዝንባሌም ነበር ብለዋል፡፡
አቶ ተስፋዓለም እንዳሉት በአዲስ አበባ አቅርቦቱ ከ60% ወደ 95% ሲደርስ አዲስ መድኃኒቶች ቀርበው ወይም የተለየ ግዢ ተፈጽሞ ሳይሆን አዲስ የኮሙኒኬሽን አሰራር ተፈጥሮ እና የጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት ጉዳይ የእኛ ምነው ብለው እንደአንድ ቡድን /task force/ በመንቀሳቀሳችን የመጣ ለውጥ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ተስፋአለም በኤጀንሲው በኩል የነበረው የፈለገው ያህል መድኃኒት ተገዝቶ ቢቀርብ የጤና ተቋማት ስራውን አብረው ካላገዙ ለውጥ አይመጣም የሚለው እምነት ትክክለኛነት በዚህ አሰራር ተረጋግጧል በማለት የባለድርሻ አካላት ለማይቋረጥ የመድኃኒት አቅርቦት ያለቸውን ቁልፍ ሚና ገልፀዋል፡፡