አገልግሎቱ በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት ተደራሽ አደረገ

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት 400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውን ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት ተደራሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡እነዚህ መሳሪያዎች በተለያየ ምክንያት ሳይገዙ የቆዩ የህክምና መሳሪያዎች መሆናቸውም ታውቋል።አገልግሎቱ የሕክምና መሳሪያ እጥረት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ስራዎች እየሰራ እንደሆነም ገልጿል።የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ውል ተገብቶባቸው ሳይገዙ የቆዩ የህክምና መሳሪያዎችን በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለተለያዩ የጤና ተቋማት እያቀረበ ነው።ከነዚህም መካከል ሰላሳ ሶስት ኤክስሬይ፣ 9 ሲቲ ስካን፣ 7 ኤም አር ማሽንና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎች ግዥ ተፈጽሞ ለጤና ተቋማት መቅረባቸውን ተናግረዋል።ተቋሙ በህዝብ የጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የህክምና መሳሪያ እጥረት በመንግስት በጀትና ከተለያዩ አካላት በሚገኝ ድጋፍ ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል።የህክምና መሳሪያዎቹ በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የምርመራ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ከፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው እንዲሁ፡፡እንድ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየሰራ ነው።አገልግሎቱ ያስመጣቸውን መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ከብክነት በጸዳ መልኩ በማከማቸት ረገድ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡የአገልግሎቱ መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች የብክነት ምጣኔ የዓለም የጤና ድርጅት ካስቀመጠው የ2 በመቶ በታች ስታንዳርድን ያሟላ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡አገልግሎቱ ከህክምና መሳሪያዎች በተጨማሪ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠና አለም አቀፍ ጥራታቸው የተጠበቀ መድኃኒትና የህክምና ግብአቶችን እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡