አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ ፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በ2023ዓ.ም በአፍሪካ ፈጣን ምላሽ ሰጪ እና ቀልጣፋ የመድኃኒቶች አቅርቦት ሰንሰለት ያለው ተቋም የመሆን ራዕይን የሰነቀው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የአቅርቦት ሰንሰለቱ ዉጤታማ እንዲሆን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ግርማ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ከጤና ተቋማት የሚላኩ የግብዓት ፍላጎት ትንበያዎች ትክክለኛ እንዲሆኑ ለማስቻል ፤ ፈጣን የሆነ የግዢ ስርዓት ለመፍጠር ፤ የመጋዘን አያያዝ ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የግብዓት ቆጠራ ሂደቱን ለማዘመንና በባርኮድ አሰራር በመደገፍ ከብልሹ አሰራር የፀዳና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ስርዓት በተሻለ ሁኔታ መፍጠር እንዲያስችል አገልግሎቱ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት መስራት አስፈላጊ ነው ሲሉ ዶ/ር አብዱልቃድር ተናግረዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታዬ ግርማ ጠቁመው ፤ የአቅርቦት ሰንሰለቱ በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆን ቴክኒካል ሞያተኞችን በማደራጀት ወደ ስራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የአገልግሎቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን ፤ ኢንስቲትዩቱ በጤናው ዘርፍ እያደረጋቸው ስላሉ ምርምሮች እንዲሁም የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለፃ ቀርቦላቸዋል፡፡
አማኑኤል ወርቃየሁ