አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ዳያስፖራው 110 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል

አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ዳያስፖራው በጦርነቱ ለተጎዱ የጤና ተቋማት 110 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ።መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ ተቋማቱን መልሶ በማቋቋም ሂደት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።ይህንን ተከትሎም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ሲሆን፤ በተለይ የህክምና ተቋማትን በግብዓት በማሟላት ረገድ በስፋት ተሳትፈዋል፡፡በዚህም 110 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የመድኃኒትና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ ገልጸዋል።ከዚህም ውስጥ 80 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የመድኃኒት ድጋፍ ሲሆን፤ 30 ሚሊዮን ብር የሚገመተው ደግሞ በህክምና ሂደት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሌሎች ቁሳቁሶች ናቸው ብለዋል።ድጋፉ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።ከዳያስፖራው የተገኘው የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተገቢውን ጥንቃቄ ወደ ጤና ተቋማት የማድረስ ተግባራት መከናወኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ዶክተር አብዱልቃድር በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና እና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይ ድጋፉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ፣ የጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ተቋማት በቅንጅት በመሆን ድጋፉን የማሰራጨት ሥራ እያከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።