ኢንሲኒሬተር የውጭ ምንዛሬ ወጪን እንደሚቀንስ ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ኢንሲኔሬተር ግንባታ ማካሄዱ ኢትዮጵያ ሃገራችን ከአሁን በፊት የዲ.ዲ.ቲ መድኃኒትን ለማስወገድ ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀርላታል ተባለ፡፡
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ዲ.ዲ.ቲን ለማስወገድ መድኃኒቱን ከገዛችበት ዋጋ በላይ ለማስወገድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ከሃገር ውጭ ታስወግድ እንደነበረ የአዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሠለሞን ንጉሤ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ሠለሞን ዲ.ዲ.ቲ እንኳን የመጠቀሚያ ጊዜው አልፎ ይቅርና መድኃኒቱ መርዛማነት ባህሪ እንዳለውና በአግባቡ ካልተጠቀምነው እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዲ.ዲ.ቲን ለማቃጠል የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንዳልነበራትና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ኢንሲኔሬተር ግንባታ ማካሄዱ ከማኅበረሠብ አልፎ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው አቶ ሠለሞን ተናግረዋል፡፡
ዲ.ዲ.ቲ ከ1100 ባላነሰ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚቃጠልና የኤጀንሲውም ኢንሲኔሬተር ማሽን እስከ 1450 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መቃጠል የሚችሉ ግብዓቶችን እንደሚያስወግድ አቶ ሠለሞን ገልፀዋል፡፡
የኢንሲኔሬተር ማሽኑ ከ1400 በላይ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚጠይቁ ጠርሙሶችና ራዲዮ አክቲቭ ወይም ጨረር አምጭ ኬሚካሎች ካልሆኑ በስተቀር ማንኛውንም መድኃኒት ማቃጠል እንደሚችል አቶ ሠለሞን አክለዋል፡፡