ኤጀንሲው ለኮሮና ቫይረስ ታካሚዎች ለመተንፈሻ አገልግሎት የሚውል መሣሪያ እያሠራጨ ነው

May 7, 2020ፊውቸርድ ዜና
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለኮቪድ 19 አገልግሎት የሚውሉ የኦክስጅን ሲሊንደሮች ስርጭት እያካሄደ መሆኑን የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ባለሙያ አቶ ጂአ ኡጋ ዛሬ ሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ገለፁ፡፡
ኤጀንሲው በመላው ሃገሪቱ ለሚገኙና የኮሮናን ቫይረስ በሽታን ለማከም ለተመረጡ 31 ሆስፒታሎች፣ 9 ጤና ቢሮዎች እና ለ2 ከተማ መስተዳድሮች 3 ሺህ 322 ብዛት ያላቸው የመተንፈሻ ሲሊንደሮች በማሠራጨት ላይ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡
ኤጀንሲው 5 አይነት የኦክስጅን ሲሊንደሮች እያሠራጨ ሲሆን አንዱ ለአንቡላንስ አገልግሎት ቀሪዎቹ ደግሞ በኮቪድ 19 ተኝቶ ታካሚዎች የሚውል መሆኑን አቶ ጂአ አብራርተዋል፡፡
የኦክስጅን ሲሊንደር አንድ ታካሚ በቂ ኦክስጅን ወደ ሠውነቱ ማስገባት ሲያቅተው ኦክስጅን ሠውነቱ ውስጥ እንዲገባ የሚረዳ የሕክምና መርጃ መሣሪያ ሲሆን ሲሊንደሮቹ 9 ሚሊየን 442 ሺህ ሃምሣ ብር ወጪ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡