ኤጀንሲው ለወባ ወረርሽኝ የሚውሉ ግብዓቶችን እያሠራጨ መሆኑን ገለፀ፡፡

ኤጀንሲው በሀገሪቱ በመጭው ጊዚያቶች ሊከሰቱ የሚችሉ ለወባ ወረርሽኝ የሚውሉ አርቲመትር + ሉሚፋንትሪን (20+120) ሚ.ግ (ኳርተም) መድኃኒቶችን እያሠራጨ እንደሆነ የክምችት አስተዳደር ባለሙያ አቶ በረከት ተዘራ ዛሬ ህዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታወቁ፡፡
ኤጀንሲው ከሕብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት በተላከለት መረጃ መሠረት ለ304 ሺህ 200 ሰዎች የሚውል መድኃኒት እያሠራጨ እንደሚገኝና ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንዳላቸው ባለሙያው አስረድተዋል፡፡
ወረርሽኙን በማስመልከት ከጤና ጥበቃ፣ ከሕብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከኤጀንሲው ሠራተኞች በማውጣጣት /Emergency Operation Center/ የኢመርጀንሲ ማእከል በሕብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት መቋቋሙን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የማእከሉ መቋቋም በሀገሪቱ ያለውን ወረርሽኝ በጋራ ተቀናጅቶ በመሥራት መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያግዝ አቶ በረከት አብራርተዋል፡፡
የወባ በሽታ በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ መሆኑንና ከሳሐራ በታች ያሉ ሀገራትን እንደሚያጠቃ ጥናቶች የሚያሣዩ ሲሆን በሽታውን ለመከላከል መድኃኒት በተረጩ አጎበሮች መተኛት እንደሚገባ ባለሙያው አሣስበዋል፡፡
በጸሎት የማነ