ኤጀንሲው በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ2012 በጀት ዓመት በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም ገለጹ፡፡
ዶ/ር ሎኮ አብርሃም በጎንደር ከተማ የተካሄደውን እቅድ ክንውን ውይይት የማጠቃለያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳብራሩት የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የተናበበ የመረጃ ሥርዓት እንዲሁም የገበያ መረጃ ኢኒሼቲቭ /market intelligence imitative / ዋነኞቹ የትኩረት ማዕከሎች አንደሆኑ ገለፀዋል፡፡
የሠራተኛውን አቅም እንገነባለን ስንል አሉ ሁሉንም የኤጀንሲውን የአቅርቦት ሠንሠለት አካላት ከጥበቃ እስከ ዳይሬክተሮች ድረስ ካሪኩለም ተቀርፆ ሰው ለሥራው የሚያስፈልገውን አቅም እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡
ሠራተኛው በአንድም በሌላም በኤጀንሲው ሥራው የሚጠይቀው ድካም /effort/ እና አደጋ /risky/ ጋር ተያይዞ በሚከፈለው ክፍያ ደስተኛ እንዳልሆነ እንደሚታወቅ ገልጸው የማትጊያ ፖኬጅ ተቀርፆ ለቦርድ በማፀደቅ ወደ ሥራ የሚገባበት ዓመት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሥራዎች ሁሉ ማዕከል የሰው ኃይላችን ነው ያሉት ዋና ዳይሮክተሩ የማትጊያ ፖኬጁ እንደ ካሁን በፊቱ ለሁሉም ሰራተኞች በጅምላ የሚሰጥ ችሮታ ሳይሆን ከመልካም አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም አፈፃፀምን መሰረት ያደረገ ኢኒሼቲቭ /performance based imitative or PBI / ስላለን በዚህ መሰረት የተሻለ አፈፃፀም ያመጣ የሚበረታተበት፣ የሚሸለምበት በአንፃሩ ያልሰራው ባለበት የሚቆይበት ነው በማለት ገልፀዋል ፡፡
ዝርዝር የአፈፃፀም መለኪያ ከቡድን ወደ ግለሰብ በማውረድ እያንዳንዱ ሰራተኛ በግለሰብ ደረጃ የሚለካ ሲሆን ለዚህም ጠበቅ ያለ የክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ መደላደል ስርዓት ይፈጠራል ሲሉ አክለዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የትኩረት አቅጣጫ የሚሆነው የተናበበ የመረጃ ስርዓት ነው ብለዋል፡፡ ከአሁን በፊት አንዳንድ ጊዜ የመረጃ ስርዓታችን እርስ በርሣችን እንዲሁም ከጤና ተቋማት ጋር መተማመን ለመፍጠር አስቸጋሪ የሆኑ ቁጥሮችን ይሰጠን ነበር፡፡ ይህ እንዳይሆን ከአንድ ቋት የተናበበ የመረጃ ስርዓት እንዲኖር ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በትኩረት የሚሰራበት አሉ ዶ/ር ሎኮ የገበያ መረጃ ኢኒቪቲሽ /market intelligence initiative/ ነው፡፡ ይህም አሰራር ቀጥታ ከህሙማን ጋር በመድኃኒት ጉዳይ የሚያገናኘን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የገበያ መረጃ ይታሰብ የነበረው ገበያው ራሱ ይመራል የሚል ሲሆን አሁን ግን አሉ እንደ ጥቁር አንበሳ ጎንደር ጳውሎስ የመሣሰሉት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ኤጀንሲው የሚያስመጣቸው ሆኖም ህሙማን የሚጠቀሙባቸው መድኃኒቶች ካሉ እነዚህን መድኃኒቶች ወደ ዝርዝራችን እናካትታለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በኤጀንሲው የግዥ መድኃኒት ዝርዝር ውስጥ ተካተው ነገር ግን የቆዩ ንጥረ ነገሮች /old molecules/ ከገበያ የምናስወጣቸው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም አሉ ዶ/ር ሎኮ በጣም ተፈላጊ የሆኑና የገበያ ጉድለት ከተከሰተ ለአብነት ሰዎች በብዛት የሚጠቀሙባቸው ታዋቂ የሆኑ ወይም ብራንድ የሆኑ መድኃኒቶች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የግል አስመጪው ሣያቀርብ ቀርቶ ህብረተሰቡ በዋጋ እንዳይጎዳ በገበያው ጣልቀ የምንገባበት አሰራር እንፈጥራለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በትልልቅ ሆስፒታሎች ላይ የመረጃ ዴስኮች ኖረው ከበሽተኛው አንደበት መረጃ የሚሰበሰብበት ስርዓትን እንከተላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህም አንድ ታካሚ ሆስፒታል ገብቶ መድኃኒት ማዘዣ ይዞ ሲወጣ ምን መድኃኒት ይዞ ወጣ እያለ ነው የለም የተባለው ወይስ ኤጀንስው ጋር እያለ ባለመናበብ የመጣ ችግር ነው አለበለዚያም ሀገር ላይ እጥረቱ ስላለ ነው የሚል መሰረታዊ መረጃ እንድንሰበስብ ይደረጋል፡፡
በከፍተኛ ህመም ለሚሰቃዩ ህሙማን እዚያው በጤና ተቋማት በአፋጣኝ /on spot/ ውሣኔ በመስጠት አቅርቦቱ እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል፡፡
እነዚህን የአቅርቦት ሰንሰለት ተግባራት ስናከናውን እርስ በርስ በመወነጃጀል ሣይሆን በተቀናጀ እና በጋራ ስንሰራ መድኃኒት የለም የሚለውን እሮሮ መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡ Supply chain of compassion!!!!!!