ኤጀንሲው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ – ጃክ ማ ኢንሽዬቲቭ በእርዳታ የተሰጠውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መመርመሪያ ኪቶችና የህክምና መገልገያዎች እያሰራጨ መሆኑን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ- ጃክ ማ ኢንሽቲቭ በመጀመሪያ ዙር በእርዳታ የተሰጠውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መመርመሪያ ኪቶችና የህክምና መገልገያዎች እየተሰራጨ መሆኑን የመድኃኒትና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች የመጋዘንና የክምችት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው መኮንን ገለጹ፡፡
እየተሰራጩ ያሉ የህክምና ግብዓቶች ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ለመለየት የሚያስችል 20,089 መመርመሪያ ኪት (Detection Kit for 2019 Novel Corona virus (2019-nCoV) RNA (PCR-Fluorescence Probing) – plastic)፣ 47,950 N95 የፊት መሸፈኛ ጭምበል፣ 1100 መከላከያ ሙሉ ፐላስቲክ ልብሶች (Disposable protective clothing – plastic)፣ 52,000 የፊት መሸፈኛ ጭምበል፣ 1000 የፊት መከላከያ ፕላስቲክ (Face Shield Guardall – plastic) መሆናቸውን አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል፡፡
ይህ በመሰራጨት ላይ ያሉ ለኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ህክምና አገልግሎት የሚውሉት መመርመሪያ ኪቶችና የህክምና መገልገያዎች የመጀመሪያው ዙር ድጋፍ አምስት ዓይነቶች ሲሆኑ በኢትዬጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትውት ጥያቄ መሰረት ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው በሁለተኛ ዙር የተሰጠው ድጋፍም በመጋዘኖቻችን ገብተው ለስርጭት ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም በቻይና መንግስት በእርዳታ የተሰጠውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ የሙቀት መጠን መለኪያ (ኢንፍራሬድን) ጨምሮ ሌሎች የህክምና ግብዓቶችን ማሰራጨቱን አስታውሰው አሁንም በጃክማ ፋዉንዴሽን ለተደረገልን የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በኢትዮጵያ መንግስትንና በኤጀንሲው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡