ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከነሐሴ 29 – 30/2011 ዓ.ም. 3ተኛውን የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ የውይይት መድረክ ከተለያዩ አካላት ጋር በጎንደር ከተማ አካሄደ፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ሙሉቀን አዳነ እንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈው ኤጀንሲው የማህበረሠብን ችግር ለመቅረፍ በመቋቋሙ ተግቶ ሊሠራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ከንቲባው መድረኩ በጎንደር ከተማ መካሄዱ ከተማውን እንደሚያነቃቃና የፌዴራል ተቋማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊታቸውን ወደ ጎንደር ማድረጋቸውን አድንቀው ጎንደርንም መርጣችሁ ስለመጣችሁ ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉቀን ኤጀንሲው ችግሮችን እየቀረፈና በውጤታማነት ለሕብረተሠቡ አጋርነቱን በተግባር ሊያሣይ ይገባል ሲሉ አሣስበዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር አሚር አማን ኤጀንሲው በርካታ መሻሻሎች እንዳሣየና ከነዚህም መካከል የማእቀፍ ግዥ በመጀመሩ በየአመቱ ይወጣ የነበረውን 110 ጨረታ ወደ 45 መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ጨረታው በአማካኝ የአንድ አመት ጊዜ ይወስድ እንደነበረና አሁን ወደ 6 ወር ዝቅ ማድረግ መቻሉንና ይህም በመሆኑ የመድኃኒት አቅርቦቱን ከ59 በመቶ ወደ 90 በመቶ በማድረሱ ሊበረታታ እንደሚገባ ሚኒስቴሩ ተናግረዋል፡፡
የማእቀፍ ግዢው የጨረታን ቁጥር ከመቀነስ ባለፈ በየዓመቱ 3 ቢሊየን ብር እንዲቆጥብ የሚያስችለው እንደሆነም ሚኒስቴሩ አብራርተዋል፡፡
ኤጀንሲው ለ3 ዓመት ከትልልቅ የአውሮፖ እና አሜሪካ ካምፖኒዎች ጋር የላብራቶሪ ሪኤጀንቶችን ለማስመጣት ኘሌስመንት በመጀመሩ ማሽኖችን በነፃ የምናገኝበትና ሪኤጀንቶችንና ኬሚካሎችን የምንገዛበት እንዲሁም ማሽኖች ሲበላሹ የሚጠገኑበት ስርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡
ከላብራቶሪ ሪኤጀንት ብቻም 450 ሚሊየን ብር መቆጠብ እንደተቻለ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ኤጀንሲው አሠራሩን በማዘመን የሲሲቲቪ ካሜራዎች፣ ጂ.ፒ.ኤስ እንዲሁም የሽረት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ማስወገጃ ኢንሲኔሬተር በ8 ቦታዎች ተከላ ማካሄዱን አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ የኢንሲኔሬተር ተከላ መካሄዱ ከውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ በተጨማሪ ለጤና ተቋማትም ትልቅ እፎይታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከ51 በላይ የካንሠር መድኃኒቶችን በየዓመቱ ማቅረብ እንደቻለና እነዚህ ስራዎች አመራሩ፣ ቋሚ ኮሚቴው፣ ቦርዱና አጋር ድርጅቶች ባደረጉት እገዛ ይህ ለውጥ በመምጣቱ እንኳን ደስ አለን ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ኤጀንሲው ይህን ሁሉ ስራ ቢሠራም መድኃኒት የለም እንደሚባልና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ተቀራርቦ መነጋገሩ የመፍትሄ ሃሣብ ለማምጣት እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡
በእለቱ ኤጀንሲው ከጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም አረንጓዴ አሻራን ለማሣረፍ የችግኝ ተከላ እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ባለድርሻ አካላት፣ የሃገር ውስጥ አምራቾች፣ የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡