ኤጀንሲው የገዛቸውን የነፍሰጡርና ፅንስ ጤንነት መከታተያ ማሽኖች ማሰራጨት ጀመረ

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ24 ሚሊየን ብር የገዛቸውን የነፍሰጡር እናቶች እና የፅንስ መከታተያ እንዲሁም የህሙማን ጤና መከታተያ ማሽኖች በስርጭት ላይ መሆናቸው ተነገረ፡፡
በኤጀንሲው ከፍተኛ የክምችት አስተዳደር ኦፊሰር አቶ እንዳልካቸው መኮንን የማሽኖቹ ብዛት 3ሺህ 600 የነፍሰጡርና ፅንስ ጤንነት መከታተያ፣ 200 የፅንስ ጤንነት (fetal monitor) እና 100 የህሙማን ጤና መከታተያ (patient monitor) መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየክልሉ ከሚገኙት ጤና ተቋማት አማራ 77፣ ኦሮሚያ 70፣ ትግራይ 40፣ ደቡብ 56፣ ሐረሪ ሁለት፣ ጋምቤላ አራት፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰባት፣ አፋር ሰባት፣ ድሬዳዋ ሁለት የነፍሰጡርና ፅንስ ጤንነት መከታተያ ማሽኖች እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
አቶ አንዳልካቸው የፌደራልና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች 24 እንዲሁም ለአዲስ አበባ ጤና ተቋማት ስድስት የነፍሰጡርና ፅንስ መከታተያ ማሽን እንደሚደርሳቸው አክለው አስታውቀዋል፡፡
የነፍሰጡርና ፅንስ ጤንነት መከታተያ ማሽኑ ለአዲስ አባባ እና ትግራይ ክልል ከሰኔ 20 ጀምሮ መሠራጨት መጀመሩን አቶ እንዳልካቸው አስታውቀዋል፡፡
የነፍሰጡርና ፅንስ መከታተያ ማሽን (Ultrasound-Doppler fetal handheld) በዕርግዝናና በወሊድ ጊዜ ያለውን የፅንስ ልብ ምት ለመከታተል ይጠቅማል ሲሉ ኦፊሰሩ አስታውቀዋል፡፡
ቀድሞ ሲሠራበት የነበረው የነፍሰጡር ፅንስ መከታተያ ማሽን በእጅ የሚሠራ መሆኑን አስታውሰው አዲሱ የእናቶችና ፅንስ መከታተያ ማሽን በድምጽ ኃይል የሚሠራ በመሆኑ ትክክለኛነቱና ውጤታማነቱ ከፍተኛ መሆኑን አቶ እንዳልካቸው አሰረድተዋል፡፡
ማሽኑ በመጠኑ ቀላል በመሆኑ እንደ ልብ በማንቀሳቀስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የፅንስ ጤንነት መከታተያ ማሽን በ6.2 ሚሊየን ብር ግዢ የተፈፀመ ሲሆን ማሽኑ የፅንሱን ጤንነት እንደሚከታተል የዝግጅት ክፍሉ ካገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡
የህሙማንን ጤንነት የሚከታተል ማሽን በ12.5 ሚሊየን ብር የተገዛ መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ተናግረው ማሽኑ የህሙማን አተነፋፈስ፣ የደም ግፊት፣ የልብ ምትና የሙቀት መጠን ይቆጣጠራል ብለዋል፡፡
ማሽኖቹ በጤና ሚኒስቴር ጥያቄ ከዘላቂ ልማት ፈንድ የተገዙ መሆናቸውን ገልጸው በወሊድ እና በዕርግዝና ጊዜ የሚፈጠረውን ሞት ለመከላከል ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ሰኔ 26 ቀን ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማሽኖቹ ከዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የእናቶችን ሞትና የፅንስ መቋረጥ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፆ እንዳላቸው አቶ እንዳልካቸው አክለው ነግረውናል፡፡