ኤጀንሲው የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል (Propoxure) እያሰራጨ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከ889 ሚሊየን 539 ሺ ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል (Propoxure) እያሠራጨ መሆኑን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ስርጭትና ተሽከርካሪ ስምሪት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሺፈራው በቀለ ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታወቁ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት መጪው የክረምት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ከወዲሁ በወባ ምክንያት የሚከሰተውን ህመምና ሞት ለመከላከል ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አከባቢዎች በአማራ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ፣ አፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ 928,011 ኪ.ግ የጸረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ዛሬ መሰራጨት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ ከ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ለወባ በሽታ መከላከያ የሚውል የመኝታ አልጋ አጎበር እየተሰራጨ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ቫይረሱ ሊያመጣቸው የሚችላቸውን አስከፊ የጤና ቀውሶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአጠቃላይ በዚህ ሁለት ወራት ውስጥ ኤጀንሲው ከ5.8 ቢሊዬን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች መሰራጨታቸውን አቶ ሺፈራው ገልጸዋል፡፡