ኤጀንሲው 1.6 ሚሊየን የወባ መከላከያ አጎበሮችን ማሰራጨት ጀመረ

May 7, 2020ፊውቸርድ ዜና
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከ3.1 ሚሊየን የወባ መከላከያ አጎበሮች ውስጥ ቀሪ 1.6 ሚሊየን ለ2 ክልሎች ስርጭት መጀመሩን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ስርጭትና ተሽከርካሪ ስምሪት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሕመድ ከድር ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ገለፁ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት እነዚህ እየተሰራጩ ያሉት የወባ መከላከያ አጎበሮች ጤና ሚኒስቴር በላከው የስርጭት እቅድ መሰረት ለጋምቤላ እና ለቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ለሚገኙ ወባማ አካባቢዎች ነው፡፡
በመሰራጨት ላይ ያሉ እነዚህ የወባ መከላከያ አጎበሮች ለሁለተኛ ዙር ሲሆን ከዚህ በፊት በየመጀመሪያው ዙር ላይ 1.5 ሚሊየን አጎበሮች ለደቡብ ክልል ለሚገኙት ሠገን፣ ወላይታ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ሸካ እና ጋሞጎፋ ዞኖች ተሰራጭቷል፡፡
ይህ እየተሰራጨ ያለው የወባ መከላከያ አጎበር GHSC-PSM /ኬሞኒክስ/ ከተባለው አጋር ድርጅት ተገዝተው የቀረቡ ሲሆን 100 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ዋጋ እንዳላቸውም ተገልጿዋል፡፡
በአጠቃላይ በሁለቱም ዙሮች የተሰራጩ እና በመሰራጨት ላይ ያሉ 3.1 ሚሊዮን የወባ መከላከያ አጎበሮች 187 ሚሊየን 395 ሺህ ብር ዋጋ እንዳላቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡