ኤጀንሲው 7ተኛው ዙር የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ግብዓቶችን አሰራጨ
የኢትዮጲያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ 7ተኛውን ዙር የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ የህክምና ግብዓቶችን ከጳጉሜ 5 አስከ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም ማሰራጨቱን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ስርጭት ቡድን መሪ አቶ ተስፋሁን አብሬ ገለጹ፡፡
ቡድን መሪው ኤጀንሲው በአገራችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በተለያዩ ዙሮች ግብዓቶችን ያሰራጨ መሆኑን አስታውሰው አሁንም ለ7ተኛ ጊዜ የግብዓቶች ስርጭት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
ከተሰራጩት ግብዓቶች መካከል 5.1 ሚሊዮን በላይ ሰርጅካል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች (Surgical face mask)፣ 90 ሺ የሚጠጋ N-95 የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች(N-95 face mask)፣ 19 ሺ የሚጠጋ face shield፣ 5 ሺ በላይ የአይን መሸፈኛ( Eye goggle)፣ Cover all with hood፣ Isolation gown እና የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘሮች (Hand sanitizer) እንደሆኑ አቶ ተስፋሁን አብራርተዋል፡፡
ሥርጭቱም በኤጀንሲው ቅርንጫፎች አማካኝነት ለሁሉም ክልሎች የተሰራጨ ሲሆን 137 ሚሊዮን 416 ሺህ 724 ብር ወጪ እንደተደረገባቸው አቶ ተስፋሁን አስታውቀዋል፡፡
ኤጀንሲው የ6ተኛው ዙር የኮቪድ 19 መከላከያ ግብዓቶችን፣ የህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶች ጨምሮ 207 ሚሊዮን በላይ ዋጋ ያላቸው መከላከያና መቆጣጠሪያ የህክምና ግብዓቶችን በነሀሴ መጀመሪያ ሳምንት ያሠራጨ መሆኑን አስታውሰው የግብዓቶቹ ስርጭትም ጤና ሚኒስቴር በላከው የስርጭት መጠን መሠረት መሆኑን ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
ሂሩት ሀይሉ