ከአገልግሎቱ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልሎት ከባለድርሻ አካላቱ ጋር ከህዳር 28 – 29/2016 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ያካሄደው የምክክር አውደ ጥናት ተጠናቀቀ፡፡
በተደረገው ምክክር የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ የተቀላጠፈ እና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በሁሉም ባለድርሻ አካላት የተለዩ የአሰራር ማነቆዎች በጋራ ተለይተው እና ምክክር ተደርጎባቸው ችግሮቹ የሚፈቱበትን የድርጊት መርሃ- ግብር በማዘጋጀት ውይይቱ ተጠናቋል።
የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አቅናው ካውዛ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበን በመስራታችን ፈታኝ ነገሮች የመኖራቸውን ያህል አዳዲስ ችግሮችም እያጋጠሙን በመምጣቱ ዛሬም እንደትላንቱ ለማህበረሰቡ ያልተቆራረጠና ቀጣይነት ያለው የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ ተቀራርቦ በመስራት የተለዩትን ማነቆዎች በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ እምነቴ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠለሞን ንጉሴ አጠቃላይ የአገልግሎቱን ስትራቴጂያዊ እቅድ አፈፃፀሞች ያስቃኙ ሲሆን አገልግሎቱ በአመቱ ውስጥ ያስመዘገባቸውን ለውጦችና ያስገኛቸውን በርካታ እውቅናዎችም አሣይተዋል፡፡
በዕለቱ አገልግሎቱ በመጀመሪያው ሩብ አመት ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በጋራ ሊሠራ ያቀዳቸውን ስራዎች አፈፃፀም እና ያጋጠሙ ማነቆዎችን የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ናሆም ገመቹ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም በሩብ አመቱ በመድኃኒት አቅርቦትና ሎጂስቲክስ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ከባለድሻ አካላቱ ጋር በሰፊው ውይይት የተካሄደ ሲሆን ችግሮቹን ለመፍታት የቀጣይ የጋራ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠው የጋራ ሀላፊነትም ወስደዋል።
በመጨረሻም ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በጋራ ተግባብቶና ተናቦ መስራት የተሣለጠ፣ ጥራቱንና ወቅቱን የጠበቀ የመድኃኒት አቅርቦትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ሲሉ የመድረኩ ተሣታፊዎች አስተያየታቸውን ሠጥተዋል፡፡
በውይይቱ ጤና ሚኒስቴር፣ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን ፣ የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በፀሎት የማነ
#ማገልገል ክብር ነው
