ከጥር 2 እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚካሄደው ለማህፀን በር ካንሰር መከላከያ የክትባት ዘመቻ መድኃኒት እየተሰራጨ መሆኑ ተገለጸ

December 30, 2021New Arrivals
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከጥር 2 እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚካሄደው ለማህፀን በር ካንሰር መከላከያ የክትባት ዘመቻ መድኃኒት በማሰራጨት ላይ እንደሆነ የመጋዘን አያያዝ ክምችት አስተዳደር ባለሙያ ወ/ሮ ማስተዋል አበባው ገለጹ፡፡አገልግሎቱ የሚያሰራጨው የክትባት መድኃኒት HPV(Human Papilloma virus) እንደሆነ ባለሙያዋ ገልጸው ክትባቱ እድሜያቸው 14 ዓመት የሆኑ ልጃገረዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ እና ከዚህ በፊት የመጀመሪያውን ዙር ለተከተቡ ልጃገረዶችም ሁለተኛ ዙር የሚሰጥ ሲሆን በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 913 ሺህ 380 ዶዝ በመሰራጨት ላይ እነደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ስርጭቱም በአገልግሎቱ በአዲስ አበባ ቁጥር 1 እና 2፣ በባህርዳር፣ በአሶሳ፣ በነቀምት፣ በነጌሌ ቦረና፣በድሬደዋ፣ በጋምቤላ፣በጅማ፣በሀዋሳ፣በአርባ ምንጭ፣በጅጅጋና በአዳማ ቅርንጫፎች አማካኝነት እየተካሄደ ሲሆን 417 ሚሊዮን 340ሺ 705 ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የክትባት መድኃኒቱም ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ብሄር ብሄርሰቦችና ህዝቦች፣ ለሲዳማ፣ ለሀረሪ፣ ለቤንሻልንጉል ጉሙዝ፣ለሶማሊያ፣ለጋምቤላ ክልሎች፣ለድሬደዋና ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እንደሚላክ የተገለጸ ሲሆን ለ858 ወረዳዎች ተደራሽ እንደሚሆን ወ/ሮ ማስተዋል ተናግረዋል፡፡
ሂሩት ኃይሉ