ከ550 ኮንቴነር በላይ መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች ወደ ኤጀንሲው መግባታቸው ተገለፀ፡፡

ኤጀንሲው ባለፋት 2 ወራት ከ550 በላይ መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ ግብዓቶችን ከሞጆ ደረቅ ወደብ ማንሣቱን የኤጀንሲው የመድኃኒት ኮንትራት አስተዳደር ባለሙያ ወ/ሮ አጋር ተስፋዬ አስታወቁ፡፡
መድኃኒቶቹ ለኤች.አይ.ቪ፣ ለሆድ ሕመም፣ ለኢንፌክሽን፣ ለስነተዋልዶ እና ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችና ሪኤጀንቶች እንደሆኑ ወ/ሮ አጋር አብራርተዋል፡፡
ወ/ሮ አጋር ከ25 ዓይነት በላይ መድኃኒቶችን ከሞጆ ደረቅ ወደብ በማውጣት በተለያዩ ቅርንጫፎችና በዋናው መ/ቤት የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘን እንደገቡ አስረድተዋል፡፡
መድኃኒቶቹንና የሕክምና መገልገያዎቹን ከሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ ተለያዩ ቅርንጫፎች በቀጥታ ማሠራጨታቸውንና ወደ ቅርንጫፍ ቀጥታ መሄዱም ጊዜንና ወጪን በመቆጠብ ለማህበረሠቡ በቶሎ መድኃኒቶችን ተደራሽ ለማድረግ ወሣኝ ሚና አለው ሲሉ ባለሙያዋ አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከባንክ የኦርጅናል ዶክመንት መዘግየት ጋር በተያያዘ ከሞጆ ደረቅ ወደብ መድኃኒቶችን በወቅቱ ለማንሣት እክል ይገጥም እንደነበረና ይህንንም ለመፍታት ኤጀንሲውና ባለድርሻ አካላቱ ተወያይተው ችግሮቹን በመፍታት መድኃኒቶቹ እንደገቡ ባለሙያዋ አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም መሠል እክሎች እንዳይከሠቱ በባንኩ፣ በሞጆ ደረቅ ወደብ፣ በኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና በኤጀንሲው መካከል ውል ለመፈራረም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ባለሙያዋ ገልፀዋል፡፡
ውሉም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኤጀንሲው ተልዕኮ ቅድሚያ በመስጠት ስራዎችን ለማሣለጥ ሠፊ ውይይት ከኤጀንሲው ጋር መካሄዱን አስረድተዋል፡፡