የሀገሪቱ 2013 በጀት አመት የመድኃኒት ፍጆታ ምጣኔ የተሻለ የፍጆታ መረጃ መሰረት በማድረግ ጤና ተቋማት ላይ ተመስርቶ ምጠና መካሄድ እንዳለበት አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ2013 በጀት አመት መቅረብ የሚገባቸው የህክምና ግብዓቶችን የተሻለ የፍጆታ መረጃ መሰረት በማድረግ እና ትክክለኛውን የምጠና ዘዴ በመጠቀም ጤና ተቋማት ላይ ተመስርቶ ምጠና መካሄድ እንዳለበት በአዳማ በተዘጋጀው ወርክሾፕ አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡
የኤጀንሲው የግዥ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ጊጋር ወርክሾፑን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በኤደንሲው መጋዘኖች መድኃኒት እያለ ጤና ተቋማት ያልተጠቀሙባቸው የህክምና ግብአቶች እንዳሉ ተናግረው በከፋተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር የሚገቡ የህክምና ግብዓቶች በመሆናቸው የ2013 ምጠና በጥራት ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም እኛና ጤና ተቋማት የበለጠ ተቀራርበን ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
የኤጀንሲው የግዥ ትንበያና ገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብይ ክፍሎም በበኩላቸው ከሚያስፈልገን በታች ምጠና ብንሠራ የአቅርቦት ክፍተት ይፈጠራል። በአንፃሩ ከምንፈልገው በላይ ምጠና ካለ ደግሞ ብክነትን ያስከትላል። ይህ እንዳይሆን የፍጆታ መረጃን መሰረት በማድረግ በጤና ተቋማት ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ምጠናው መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
አቶ አብይ አክለውም ምጠና/quantification/በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ የመጀመሪው ተግባር መሆኑን ገልጸው ምን አይነት እና ምን ያህል መድኃኒቶች ያስፈልጉናል፤ እነሱን ለመግዛት ምን ያህል በጀት እንደሚበቃ በመገመት ምጠናውን ማካሄድ እንደሚጠበቅ ገልጸው ይህም በወቅቱ ግዥ ለመፈፀጸም ያስችላል ብለዋል፡፡
በቅርንጫፎች እና በክላስተር የተዋቀረው ቡድን ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መረጃዎችን በመሠብሰብ፣ በመተንተን እና አደራጅቶ እስከ ጥር 30 ለማዕከል በመላክ ዋና መ/ቤቱም ከየ ክላስተሩ የመጡትን መረጃዎች አይቶና እንደገና በውይይት ከዳበረ በሗላ የሀገሪቱ የቀጣይ አመት የመድኃኒት ፍጆታ ምጣኔ/quantification /ይሰራል ብለዋል።
ወርክ ሾፑ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከኤጀንሲው የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ሀላፊዎችና ሙያተኞች በአጠቃላይ ወደ 75 ተሳታፊዎች በምጠና መርሆዎችና ዘዴዎች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን እስከ ጥር 30/2012 ተገቢ መረጃ ተሰብስቦ የተጣራ ምጠና ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
Supply chain of compassion!!!!!!!!!