የላብራቶሪ የሲቢሲ እና የኬሚስትሪ ማሽኖችን የCovid -19 ህክምና ለሚሰጡ ማዕከላት በማሰራጨት ተከላ ማከናወን ጀመረ

May 27, 2020ፊውቸርድ ዜና
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ለ Covid -19 ታካሚዎች የደም ምርመራ ማከናወኛ የላብራቶሪ የሲቢሲ እና የኬሚስትሪ ማሽን በማሰራጨት ተከላ ማከናወን መጀመሩን የክምችት አስተዳደር ባለሙያ ወ/ሮ ሚዛን ገ/ዮሐንስ ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ገለጹ፡፡
በክልል ጤና ቢሮዎች እና በሆስፒታሎች ጥያቄ መሰረት ለሚሊኒየም አዳራሽ፣ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ለሞጆ፣ ለበቆጅ፣ ለሞያሌ፣ ለባሌ ሮቤ ሆስፒታሎች፣ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ለሁመራ፣ አክሱም፣ ዓዲግራት እና መለስ አካዳሚ ሆስፒታሎች በአጠቃላይ 9 ማሽኖችን ስርጭት መካሄዱን ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡
ለሞጆ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል Cobas C 311 የተሠኘ የላብራቶሪ ማሽን ተከላ የተካሄደ ሲሆን ከ400 ሺ ብር በላይ ወጪ ያላቸውን ሪኤጀንቶች ለሆስፒታሉ ተሠራጭቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ወ/ሮ ሚዛን አስረድተዋል፡፡
የሕክምና መሣሪያው የጉበት፣ የኩላሊት፣ የስኳር በሽታና ሌሎችም ምርመራዎችን ለማከናወን የሚያገለግል መሆኑ ባለሙያዋ አክለው ገልጸዋል፡፡