የመድኃኒትናየህክምናመገልገያዎችመጋዘን አያያዝናክምችትአስተዳደርመመሪያ ክለሣ ተካሄደ፡፡
በአገልግሎቱ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች መጋዘን አያያዝና ክምችት አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ ላይ የአገልግሎቱ ማኔጅመንት አባላት መጋቢት 9 ቀን 2016 ውይይት ተደርጓል፡፡
ከዚህ በፊት ለረጅም አመታት ስንገለገልባቸው ከነበሩት አንዱ የውስጥ አሰራር፣ የመጋዘን እና ክምችት አስተዳደር መመሪያ ሲሆን ይህ መመሪያ እጥረቶች ያሉበት በመሆኑ አዳዲስ አሠራሮች ተካተው ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሌሎችም ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች የክምችትና ስርጭት አስተዳደር ዘርፍ መመሪያዎች እየተከለሱና እየተዘጋጁ መሆኑንም አክለዋል።
በ6 ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ እና በውስጡ ዝርዝር የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች መጋዘን አያያዝና የክምችት አስተዳደር ተግባራትን በዘመናዊና በተቀናጀ መንገድ ለማከናወን የሚረዱ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡
በአንድ በኩል የመጋዘን አያያዝና ክምችት አስተዳደር በአገልግሎቱ የአሰራር መርህ መሰረት እንዲፈጸም፤ የመድኃኒት ክምችት በዕቅድ እንዲመራ፤ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የመድኃኒትና መጋዘን አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር፤ አግባብነት ያለዉ ርክክብና ክምችት አያያዝ የሚያስፈልጉ መዛግብትና ደረሰኞች በመጠቀም የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግ አላማ አለው፡፡
በሌላ በኩል በየደረጃው ያለውን ክምችት በዘመናዊ አሰራር በቀላሉ ለማየት፣ ለማወቅና ለመከታተል የሚያስችል ስርዓት እንዲኖር ማድረግ፤ ለጤና ተቋማት የሚደርሱ መድኃኒቶች ደህንነታቸው እና ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ፤ የመድኃኒት ብክነት ለመቀነስ የሚያስችል ዘመናዊ የመጋዘን አደረጃጀት፣ ክምችት አያያዝና አስተዳደርን ማስፈን አላማዎች እንዳሉት በውይይት ወቅት ተገልጻል፡፡
ለአንድ ጤና ተቋም በአገልግሎቱ በክምችት የሌሉትን ወይም የማይገኙትን ጤና ተቋማት ከሌሎች አማራጭ መግዛት እንዲችሉ የህክምና ግብዓቶች አለመኖራቸውን ማስረጃ /Stock out Certificate/ የሚሰጥበትን አሰራር የተቀመጠ ሲሆን በተገላባጭ ፈንድ ተገዝተዉ የሚቀርቡ ግብአቶች መንግስታዊ ላልሆኑና የግል የጤና ተቋማት ስለሚስተናገዱበት አሰራር ያካተተ መመሪያ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በዋናዉ መ/ቤትና በቅርንጫፎች በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ ክምችት ያላቸው መድኃኒቶች የአደራ ሽያጭ (Consignment) መፈጸም የሚቻልበትን አሰራር ያካተተ ነው።
ረቂቅ መመሪያው ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች እና ባላድርሻ አካላት ተሳትፈውበት በውይይት ከዳበረ በኋላ በአገልግሎቱ የስራ አመራር ቦርድ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡
