የመድኃኒት አቅርቦቱን ለማሻሻል ከጤና ሚንስቴር ጋር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ፡፡ —————————————-

በሃገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት የመድኃኒት ፍላጎት ትንበያ /Forecast/ በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ ካልሆነ በኤጀንሲው ሀገራዊ የመድኃኒት ፍላጎት ትንበያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል የመድኃኒት ግዢ ትንበያና የገበያ ጥናት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ዘበነ ገለጹ፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለጻ የጤና ተቋማት የመረጃ አያያዝ ድክመት ከባለፈው የተጠቀሙትን መነሻ በማድረግ የወደፊት ፍላጎታቸውን ለመተንበይ ስለሚቸገሩና እንዲሁም ለመድኃኒት ግዥ የሚመደብላቸው በጀት አነስተኛ መሆን ፍላጎታቸውን ከበጀታቸው ጋር ለማጣጣም ሲሉ የሚያደርጉት ማስተካከያ በሀገራዊ ትንበያው ትክክለኛነት ላይ ተፅእኖ እንደሚያሣድር አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የመድኃኒት የግዥ ጥያቄ ሲቀርብ ግዥውን ለማከናወን የሚወስደውን ጊዜ (Procurement lead time) ያገናዘበ የግዥ እቅድ ቢዘጋጅም ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና አቅራቢዎች በወቅቱ በውላቸው መሰረት መድኃኒቶቹን አለማቅረባቸው ተደምሮ ግብዓቶቹ በታቀደው ጊዜ ስለማይገቡ ለግዥ ትንበያው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስተባባሪው አክለው ገልጸዋል፡፡
ችግሮቹን ለመቅረፍ አብዛኞቹን የህክምና ግብዓቶች በማእቀፍ ግዥ እየተፈፀሙ በመሆኑ የመድኃኒት ግዥ ሂደቱን ከማሳጠሩም ባሻገር ወቅታዊ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ በማእቀፍ ግዢ ውል ከተገባው አቅራቢ በድጋሚ ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልግ የግዥ ትእዛዝ በመስጠትና ግብዓቱ በወቅቱ እንዲገባ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የጤና ተቋማትም ሀገራዊ የግዥ ትንበያውን ትክክለኛነት ለማሻሻል የመረጃ አያያዛቸውን በማጠናከርና የሚመደብላቸው በጀትም ዓመታዊ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተባብረው እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ ጉልላት ተናግረዋል፡፡
የመድኃኒት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም በአቅርቦት ሠንሠለት ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ቡድን መሪው አሣስበዋል፡፡