የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን መሰረታዊ ችግሮች የሚቀርፍ እና ለሀገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ልዩ #የግዥ መመሪያ ፀድቆ ወደ ስራ ገባ።
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
በመመሪያ ቁጥር 1066/2017 ዓ.ም መሰረት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በማዕከል የሚፈፀሙ የመድኃኒት እና የህክምና መሣሪያዎች የግዥ አፈፃፀም መመሪያን ተግባራዊ በማድረግ ቀልጣፋና በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት ሰጪ ተቋም እየገነባ እንደሆነ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በአገልግሎቱ ዋና መስሪያ ቤት ለሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ የሚድያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን መሰረታዊ ችግሮች የሚቀርፍ እና ለሀገር ውስጥ አምራቾች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ልዩ የግዥ አዲስ #መመሪያ ፀድቆ ወደስራ ተገብቷል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በማዕከል የሚፈፀሙ የመድኃኒት አቅርቦት እና የህክምና መሳሪያዎች የግዥ አፈፃፀም መመሪያን በፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 ዓ.ም አንቀፅ 87 ንዑስ አንቀፅ 3 መሰረት ለገንዘብ ሚኒስቴር በተሰጠው ስልጣን ልዩ የግዥ መመሪያ በማፀደቅ ወደ ስራ መግባቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የተለየ የመድኃኒት የግዥ መመሪያ ያስፈለገበትን ምክንያት ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩ ሲሆን ለተለዋዋጭ የጤና ፍላጎት ፣ ለሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የማህበረሰብ የጤና መድህን ተጠቃሚ ፍላጎት ወቅታዊና ፈጣን ምላሽ ከመስጠት እና የመድሃኒት ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር መንግስት የሃገር ዉስጥ የመድሃኒት አምራቾችን ለማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም መድሃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች ከግዥ አፈፃፀማቸው ጀምሮ እስከ አጠቃቀማቸው ልዩ ጥንቃቄ የሚጠይቁ በመሆኑ ፤ ይህንን ልዩ ባህሪ ታሳቢ ያደረገና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስትራቴጂያዊ የግዥ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የግዥ መመሪያው በዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ግዥ መፈፀም የሚቻልበት የገንዘብ ጣሪያ (Threshold Limit) 3 ቢሊዮን ብር መደረጉን ፤ የዉስን ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ 2 ቢሊየን ብር እንደሆነ ፤ የጨረታ ቆይታ ጊዜ (Floating Period) ለብሔራዊ ግልፅ ጨረታ 15 ተከታታይ ቀናት ፤ ለዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ 21 ተከታታይ ቀናት እና ለዉስን ጨረታ ደግሞ 10 ተከታታይ ቀናት እንደሆነ መመሪያው ከአሁን በፊት ለግዥ ይወስድ የነበረውን ጊዜ (procurement lead time) በከፍተኛ ደረጃ ያሳጠረው መሆኑን ዶ/ር አብዱልቃድር አስረድተዋል፡፡
መመሪያው የሀገር ዉስጥ አምራቾችን በእጅጉ የሚያበረታታ እና ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የረጅም ጊዜ የአቅርቦት ዉል በማስገባት ጥሬ እቃ በሀገር ዉስጥ በመጠቀም እንዲያመርቱ እድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም በሀገር ውስጥ አምራቾች ግብአቶች መቅረብ ካልተቻሉ ከውጭ ገበያ ለሟሟላት አማራጭችን (Options) አስቀምጧል።
በመጨረሻም የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም መመሪያውን ከጅምሩ አንስቶ እስኪፀድቅ ንቁ ተሳትፎ ለነበራቸው ልዩ ልዪ ባለድርሻ አካላት ዋና ዳይሬክተሩ በተቋሙ ስም ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡
#ማገልገል ክብር ነው!
