የምስራቅ ክላስተር የ1.4 ቢሊየን ብር መድኃኒቶችን ማሠራጨቱ ተገለፀ፡፡

የምስራቅ ክላስተር በ2011 በጀት ዓመት ከ1.4 ቢሊየን ብር በላይ የሆኑ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ማሠራጨቱን ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በተካሄደው 3ተኛው የአቅርቦት ሠንሠለት መድረክ አስታወቀ፡፡
በበጀት ዓመቱ በተገላባጭ ፈንድ 229.9 ሚሊየን ብር ወጪ ያላቸው መድኃኒቶችና 1.2 ቢሊየን ወጪ ያላቸው የኘሮግራም መድኃኒቶች መሠራጨታቸውን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሣሙኤል ኃይሉ አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የወለል ጥገና መካሄዱ፣ የሲ.ሲ.ቲ.ቪ ካሜራና የጂ.ፒ.ኤስ መገጠም፣ የክትባት መድኃኒቶችን በወቅቱና የቀጥታ ስርጭት ማካሄዱ እና የፈጣን ለውጥ አምጭ ሥርዓት ትግበራ በውጤታማነት ማካሄዳቸውን አቶ ሣሙኤል ተናግረዋል፡፡
ሌላው ኤም. ብራናን በ35 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ማድረጋቸውን፣ ከሀገር ውስጥ አምራቾች ጋርም መደበኛ የውይይት ጊዜ እንደነበራቸውና የሠራተኞች እርካታ ዳሠሣ ጥናትንም እንዳካሄዱ ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
ክላስተሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቴሌግራም፣ ቫይበር፣ ፌስ ቡክ፣ ዋትስ አኘ እና ዌብሣይትን ለመረጃ ልውውጥ ተጠቅመናል ብለዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም. ለክላስተሩ 22.5 ሚሊየን ብር ተበጅቶ 19.5 ሚሊየን ብር ወይንም 89 በመቶውን መጠቀማቸውን ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በጅጅጋና በድሬዳዋ ቅርንጫፍ የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘን ጥበት፣ የአንዳንድ መድኃኒቶች አለመኖርና የአስተሻሸግ ችግር እንዳጋጠማቸው ሪፖርቱ ያሣያል፡፡
የምስራቅ ክላስተር በቀጣይ በጀት ዓመት የልህቀት ማዕከል ትግበራ እና የፈጣን ለውጥ አምጭ ስርዓትን የማጠናከር ስራዎችን ለመስራት እንዳሠበ ተናግሯል፡፡
የምስራቅ ክላስተር የኤጀንሲውን 3 ቅርንጫፎች ድሬዳዋ፣ ጅጅጋ እና ቀብሪድሃርን እንደሚያጠቃልል፣ በክላስተሩ 24 ሆስፒታሎችና 377 ጤና ጣቢያዎችን ተደራሽ እንደሚያደርጉና 238 የሠው ኃይል መኖሩን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡