የተገላባጭ ፈንድን ለማሳደግ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ፡፡ ===================================

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ2011 በጀት ዓመት የተገላባጭ ፈንድ /RDF/ ለማሳደግ በተያዘው እቅድ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ከዱቤ ሽያጭ መሰብሰብ እንደተቻለ የኤጀንሲው የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋ/ ዳይሬክተር አቶ መሐሪ ተከስተ ገልጸዋል፡፡
ለጤና ተቋማት የዱቤ ሽያጭ ከተሰጠው ብር 2 ቢሊየን 350 ሚሊየን 146 ሺህ 243 ብር ከ68 ሣንቲም ውስጥ ብር 1 ቢሊየን 815 ሚሊየን 176 ሺህ 561 ብር ከ61 ሣንቲም መሰብሰብ እንደተቻለ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የጤና ተቋማት ያለ ገደብ ከኤጀንሲው በርካታ የጤና ግብዓቶችና የህክምና መገልገያዋች በዱቤ ሽያጭ ይወስዱ እንደነበር አቶ መሐሪ ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ግን በብድር ላይ ብድር የማይስተናገድበትን አሠራር እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡
ይህ አሠራር የጤና ተቋማት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችን የተሻለ በጀት ጠይቀው እንዲያዝላቸው ከማድረጉም በላይ ያለባቸውን ውዝፍ ከፍያ እንዲመልሱ እድል ፈጥሯል ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የተገላባጭ ፈንድ መጠኑን ለመጨመር ኤጀንሲው ቀደም ሲል የተጠናከረ የበጀት ሥርዓት ያልነበረው ሲሆን ባለፈው እና በያዝነው በጀት ዓመት በጥናት ላይ የተመሰረተ በጀት እንዲዘጋጅና እያንዳንዱ ሥራ የተያዘለትን በጀት ተከትሎ እንዲፈጸም ተደርጓል ብለዋል፡፡
የተመደበውን በጀት ለመከታተል እንዲቻልና ወጪ የሚያንሩ አሠራሮችና የሥራ ክፍሎችን በመለየት ማስተካከያ መውሰድ እንዲቻል ‹‹Management Accounting Team›› በማቋቋም የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ከአቶ መሐሪ ገለጻ ማወቅ ተችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ወጪ ለመቀነስ ኤጀንሲው ባለው ንብረት በአግባቡ እንዲጠቀም በማድረግ ከፍተኛ ወጪ የመቀነስ አሠራር እየተተገበረ እንዳለ አክለው ገልጸዋል፡፡
Supply chain of compassion!!!