‹‹የኤጀንሲው ቅርንጫፎች የአተት ወረርሺኝ በተከሰተባቸው ቦታዎች የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶችን እያደረሱ ነው››
የአተት /ኮሌራ/ ወረርሺኝን ለመከላከል ኢጀንሲው በቂ የመድኃኒት ክምችት አለው።
“””””””””””””””””””””””””””””””“””””””””””
የአጣዳፊ ተውከትና ተቀማጥ /ኮሌራ/ ወረርሽኝን ለመከላከል የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በቂ መድኃኒት ክምችት እንዳለው እና ግብዓቶችን እያሰራጨ መሆኑን የክምችትና ሥርጭት አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ከፍተኛ የአቅርቦት ሠንሠለት አማካሪ አቶ ዱፌራ ንግሣ አስታወቁ፡፡
እስካሁን ወረርሽኙን ለመከላከል በሽታው ይከሰትባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ቦታዎችን በመለየት የሚመለከታቸው የኤጀንሲው ቅርንጫፎች እንዲዘጋጁ ተደርጓል ሲሉ አቶ ዱፌራ በዛሬው እለት ተናግረዋል፡፡
አማካሪው በአሁን ሰዓት በቂ የመድኃኒትና ለበሽታው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ክምችት እንዳለ አስታውቀው ቅርንጫፎችም ራሳቸው ወረርሽኙ ወደተከሰተባቸው ቦታዎች የመድኃኒትና ህክምና ግበዓቶች እያደረሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዲስ አበባ ለሚገኙ ሰባት የጤና ተቋማት የህክምና ግብዓቶች እንዲደርስ በጠየቀው መሠረት መድኃኒቶችን ለማድረስ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ዱፌራ ተናግረዋል።
አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ በሚሰጠው ጥቆማ መሠረት ወረርሺኙ ሊከሰት የሚችልባቸው አካባቢዎች በአቅራቢያው በሚገኙ የኤጀንሲው ቅርንጫፎች ሊስተናገዱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በኤጀንሲው ድንገተኛ ችግሮችን የሚከታተል ቡድን እንዳለ አማካሪው አስታውቀው ወደ ኤጀንሲው ለሚመጡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አማካሪው ወረርሺኙን ለመከላከል የሚያግዙ መድኃኒቶች በጣም ከሚፈለጉ የመድኃኒት ግብዓቶች መካከል መሆናቸውን አውስተው መድኃኒቶቹ በሀገር ውስጥ አምራቾችም ጭምር የሚመረቱ በመሆናቸው የክምችት መጉደል ስጋት እንደማያጋጥም አስታውቀዋል፡፡
የአጣዳፊ ተውከትና ተቅማጥን ለመከላከል የሚረዱ 14 መድኃኒቶች እንደተለዩ የተነገረ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሪንገርላክቴት፣ ኖርማል ሳላይን እና ዶክሲሳይክሊን ይገኙበታል፡፡