የኤጀንሲው ጎንደር ቅርንጫፍ ሰብል በመሰብሰብ አቅመ ደካሞችን እየረዳ መሆኑን ገለፀ፡፡ ========================

የኤጀንሲው ጎንደር ቅርንጫፍ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት እየተበላሸ የሚገኘውን የጤፍ ሰብል በመሰብሰብ የአካባቢውን አቅመ ደካሞች እየረዳ እንደሚገኝ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለው አስማማው ገለጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ ዛሬ ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ከዝግጅት ክፍሉ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት በአሁኑ ሰዓት የቅርንጫፉ የመጋዘን ወለል ጥገና እየተደረገ እንደሚገኝና የሥራ ጫና እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
ሠራተኞቹ የሥራ ጫና በሌለበት በዚህ ወቅት ይህን በጎ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ ሀሳቡን አፍልቀው በፍቃደኝነትና በራሳቸው ተነሳሽነት ከህዳር 17 ቀን ጀምረው እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ይህ በጎ ተግባር የሚከናወነው ብዛታቸው 10 ለሚደርሱ አቅመ ደካሞች መሆኑን የገለጹት አቶ እንዳለው የአንዱ ገበሬ ማሳ ከ5 እስከ ስድስት ሄክታር እንደሚደርስና በ2 ቀናት ውስጥ ከ3 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የጤፍ ሰብል መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የተሰበሰበው የጤፍ ሰብል በጉልበት ዋጋ ሲተመን በግምት 14,400 ብር እንደሚሆን ሥራ አስኪያጁ ገልጸው በ2 ቀናት ውስጥ 120 ሰው የተሳተፈበት ሥራ ሰብሉ ተነስቶ እስከሚያልቅ ድረስ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የዚህ በጎ ተግባር ክንውን ጠቀሜታው ለገበሬዎቹ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያስከትለውን ጉዳት በጋራ ተቀናጅቶ በመሥራት ችግሩን ለመቋቋም እንደሚያግዝ አቶ እንዳለው አክለው አብራርተዋል፡፡