የግሎባል ኸልዝ ኢኒሼቲቭ ልዑካን ቡድን በሲዳማ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማትን ጎበኙ

የጤና ሚኒስቴር የልማት አጋር ድርጅቶች ጥምረት የሆነው የግሎባል ሄልዝ ኢኒሼቲቭ ልዑካን ቡድን አባላት በሲዳማ ክልል የሚገኙትን የሞቲቴ ፉራ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ሀዌላ ቱላ ጤና ጣቢያ፣ ቁልባ ጤና ኬላ እና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሐዋሳ ቅርንጫፍን ጎብኝተዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ለልዑካን ቡድኑ የክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ስርዓት ትግበራ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ እየተገበራቸው የሚገኛቸው ኢኒሼቲቮችን ማጠናከር፣ የህክምና እና የመድኃኒት አቅርቦትን ማሳደግ፣ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ስራዎችን ማስቀጠል፣ እና የጤና ፋይናንስን ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ከልዑካን ቡድኑ አባላት ጋር ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር አጋር ድርጅቶች በሲዳማ ክልል በመገኘት የጤና ተቋማትን መጎብኘታቸው ለኢትዮጵያ የጤና ስርዓት መጠናከር የሚያደርጉት ድጋፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋፆ በአካል እንዲያዩ ያስቻለ መሆኑን የገለጹት በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር መብራቱ ማሴቦ ጉብኝቱ አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መተማመኛ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች የህብረተሰቡን ጤና በማሻሻል በኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያግዝ መመልከታቸውን የልዑካን ቡድኑ አባላት የተናገሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሐዋሳ ቅርንጫፍ ዲጂታላይዝድ የሆነ ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት መቻሉን አድንቀዋል፡፡