የግሎባል ፈንድ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ አገልግሎቱን ጎበኙ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር በአጋርነት ከሚሰሩ በርካታ አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል በዋነኝነት ግሎባል ፈንድ ይጠቀሳል ፤ ግሎባል ፈንድ የጤናውን ዘርፍ በመደገፍ ቁልፍ አጋር ሲሆን የግሎባል ፈንድ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ በአገልግሎቱ የካቲት 8/2017 ዓ.ም ጎብኝተዋል ፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ አገልግሎቱ ያለውን ተቋማዊ መዋቅር ፣ የህክምና ግብዓቶች የክምችት መጠን ፣ የፋይናንስ አሰራር ፣ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ፣ የግሎባል ፈንድ መዋዕለ ንዋይ በአገልግሎቱ ምን እንደሚመስል ፣ ከአጋር አካላት ጋር ያለው የግንኙነት ሁኔታ ፣ የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ የትግበራ ሂደት ፣ የቀጥታ ስርጭት አቅርቦት መሻሻል ፣ የፀደቀው አዋጅ የሚያመጣቸውን ለውጦች ፣ ወረቀት አልባ የቢሮ አገልግሎት የመስጠት ሂደት በዝርዝር አቅርበው ከጎብኚዎች የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ያደረጉት ጉብኝት ውጤታማ መሆኑን የግሎባል ፈንድ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ ተናግረው ፤ እ.ኤ.አ በ2019 አገልግሎቱን መጎብኘታቸውን አስታውሰው ከፍተኛ ለውጥ መመልከታቸውን በተለይም የቆጠራ ትክክለኝነት ፣ የተቀናጀ የመረጃ አሰራር ስርዓት የትግበራ ሂደት(ERP Implementation) ፣ የቀጥታ ስርጭት አቅርቦት መሻሻል ፣ የፀደቀው አዋጅ የሚያመጣቸውን ለውጦች ፣ አጠቃላይ የአገልግሎቱ የአፈፃፀም መሻሻሉን ጠቅሰዋል ፡፡
ከኢትዮጵያ ብሎም ከጤና ሚኒስቴር ጋር የቆየና ጠንካራ አጋርነት እንዳላቸው ፒተር ሳንድስ አስታውሰው በቀጣይ በርካታ ስራዎችን መስራት እንቀጥላለን ብለዋል ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው፤ ግሎባል ፈንድ ባደረገው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ የመድሃኒት አገልግሎትን የሚያዘምን ዲጅታል ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።
ማገልገል ክብር ነው !
ማኅሌት አበራ