ደሴ ቅርንጫፍ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የኢትዮጵ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደሴ ቅርንጫፍ በጦርነት ከወደመ እና ከተዘረፈ በኋላ በተደረገው ርብርብ ከጥር 16/2014 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱል ቃድር ገልጋሎ ገለፁ፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ 190 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ወደ ቅርንጫፍ ደርሰው ለጤና ተቋማት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ለእናቶችና ለህፃናት የሚውሉ የህክምና ግብዓቶችን ጨምሮ ለስኳር እና ለደም ግፊት ህሙማን የሚውሉ መድኃኒቶች እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
በአከባቢው በነበረው ጦርነት የወደመውንም ሆነ የተዘረፉትን የቅርንጫፉን ሀብቶች የሚያጠና ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝርዝር ጥናት እየተደረገ ነው ያሉት ሀላፊው ዋናው ነገር ቶሎ የቅርጫፉን አገልግሎት ማስጀመር ትልቅ ትኩረት ያደረግንበት ጉዳይ ነበር ብለዋል፡፡
ስለዚህም ያሉንን ቅርንጫፎች በማስተባበር ለህክምና ግብዓቶች ማከማቻ መጋዘኑ የሚያስፈልጉትን የስራ መሳሪያዎች በፍጥነት እንዲሟሉ የተደረገ ሲሆን በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉትንም ተገዝተው እንድሟሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የጤና ተቋማት ተገቢውን መድኃኒት በቶሎ ማግኘት አለባቸው ያሉት ዶ/ር አብዱልቃድር በቅርንጫፍ ላይ የደረሰውን የመሰረተ ልማት ውድመት እንደገና በማልማት በቀጣይ ስራወች ተሠርተው የሚሟላ ይሆናል ብለዋል፡፡
በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ዝርፊያና ውድመት የደረሰበት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ደሴ ቅርጫፍ ለ27 ሆስፒታሎች፣ ለ303 ጤና ጣቢያዎች፣ ለ60 ወረዳዎች ከ8.7 ሚሊዮን ህዝቦች በላይ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ የተደራጀ ቅርጫፍ እንደነበር ይታወቃል።
አወል ሀሰን