ለዓለም አቀፍ የህክምና ግብዓት አቅራቢዎች እዉቅና ተሰጠ
በ3ኛዉ አለም ዓቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ 25 ለሚሆኑ ዓለም አቀፍና የሀገር ዉስጥ የህክምና የግብዓት አቅራቢዎች የክሪስታል ዋንጫና ሰርተፍኬት ሽልማት በስካይ ላይት ሆቴል የተሰጠ ሲሆን፤ የመድኃኒት ተደራሽነቱ እንዲሳለጥ ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።
በምርጥ 20 እና 10 አቅራቢዎች ለመሸለም በመመዘኛ መስፈርትነት የነበረው የመድኃኒት ማቅረቢያ ጊዜ፤ የግዥ ትእዛዝ መጠንን በሙሉ ከማቅረብ፣ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት፣ ከአገልግሎቱ ዓመታዊ ግዥ የአቅራቢው የአቅርቦት ድርሻ በገንዘብ፣ የቀረበ የመድኃኒት አይነት ብዛት እንዲሁም የቀረበው የግዥ ትእዛዝ ብዛት በማወዳዳሪያ መስፈርትነት እንደተለዩ የሽልማት ኮሚቴዉ ገልጿል።
የህንድ ኩባንያዎች ከፍተኛውን የሽልማት ድርሻ ያገኙ ሲሆን የቻይና፣ የጀርመን፣ የቆብሮስ፣ የዴንማርክ፣ የኬኒያ እና የኢትዮጵያ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አውቅና ተሠጥቷቸዋል።
ሀገር ፈተና በገጠማት ወቅት ፈጣን ምላሽ በመስጠት፣ ከፍተኛ መጠን ያለውን የህይወት አድን የህክምና ግብአት በማቅረብ እንዲሁም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ፋብሪካ ገንብተው የውጭ ምንዛሬ ያዳኑ በልዩ ተሸላሚነት ለ5 አምራቾች አውቅና ተሰጥቷል።
በዚህ የሽልማት ዘርፍ ሂዩማን ዌል ፋርማሲቲካል ኢትዮጵያ ሊሚትድ በሀገር ውስጥ መድኃኒት ዘርፍ ከፍተኛ መዋል ንዋይ በማፍሰስ ህይወት አድን መድኃኒት በማቅረቡ፣ ጉሊን ኤች.ቢ.ኤም ፕሮቴክሽንስ /ቻይና/ ከፍተኛ መጠን ያለውን የህክምና መገልገያ በአጭር ጊዜ በማቅረቡ፣ አዳማ ዲቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /ኢትዮጵያ/ በሀገር ውስጥ መድኃኒት ዘርፍ መዋል ንዋይ በማፍሰስ ከፍተኛ መጠን ያለውን ለህክምና አገልግሎት የሚውል ፋሻ በሀገራዊ ጥሪ በአስቸኳይ ጊዜ በማቅረቡ፣ ፍሬሲኒየስ ካቢ /ጀርመን/ ከፍተኛ መጠን ያለውን የህይወት አድን መድኃኒት በአጭር ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ በማቅረቡ፣ ፋርማኪውር /ኢትዮጵያ/፡ ህይወት አድን መድኃኒትን አስቸኳይ ጊዜ በማቅርቡ ልዩ ተሸላሚዎች ሆነዋል።
