የቅድሚያውልየሚገባበትየአቅርቦትሥርዓትአፈጻጸምመመሪያ
የተከበራችሁ ደንበኞቻችን የእናንተ አስተያየት በመመሪያው ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ቀጥሎ በተጠቀሰው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከመጽደቁ በፊት አስተያየት እንዲትሰጡን በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡
መመሪያ ቁጥር …. /2017
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት
የቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት አፈጻጸም መመሪያ
www.epss.gov.et
መመሪያ ቁጥር …. /2017
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት
የቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት አፈጻጸም መመሪያ
ግንቦት/2017
ጤና ተቋማት ለአገልግሎቱ የሚያቀርቡት የመድኃኒት ግዥ ጥያቄ ወቅታዊ፣ትክክለኛ ምጠና ላይ የተመሰረተ እና በበጀት የተደገፈ በማድረግ የግዥና ስርጭት መዘግየትን፣የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትን እና ብክነትን በማስቀረት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
የመድኃኒት አቅርቦትን የቅድሚያ ውል በሚገባበት የአቅርቦት ስርዓት በመደገፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ እንዲቀንስ በማድረግ የአገልግሎቱን የአቅርቦት አቅም ማሳደግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የመሰረታዊ መድኃኒቶችን ፍላጎትና አቅርቦት አጣጥሞ በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ለጤና ተቋማት ለማቅረብ እያገጠመ ያለዉን ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና ከጤና መድህን ትግበራ ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት የመድኃኒት አቅርቦት በዘላቂነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ፤
በጤና ተቋማት ጥራት ያለው የመድኃኒት ምጠና ማከናወን እና በተረጋገጠ በጀት መሰረት ብቻ የግዢ ውል የመግባትና ግዢ የማከናወን ስርአት መዘርጋት በማስፈለጉ፤
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትና ፈንድ ማቋቋሚያ በአዋጅ ቁጥር 1354/2017 አንቀጽ 28 (2) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
1. አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ “የቅድሚያ ውል የሚገባበት የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት አፈጻጸም መመሪያ” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፤
2. ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ ፤-
- “አዋጅ” ማለት በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትና ፈንድ ማቋቋሚያ በአዋጅ ቁጥር 1354/2017 ነው፡፡
- “አገልግሎቱ” ማለት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ነው፤
- “ጤና ተቋም” ማለት የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ ለመስጠት የተቋቋመ ማንኛውም የመንግስት ወይም ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፤
- “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ-መንግስት አንቀፅ 47 መሰረት የተቋቋመ ክልል ሲሆን፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ይጨምራል፤
- “ጤና አስተዳደር” ማለት የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮ፣ የዞን ጤና መምሪያ፣ የወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት፣ የከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ፤ የክፍለ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤትን ያካትታል፤
- “ሚኒስቴሩ” ወይም “ሚኒስትር” ማለት እንደ ቅደም ተከተሉ የጤና ሚኒስቴር ወይም ሚኒስትር ነው፤
- “መድኃኒት” ማለት የሰውን በሽታ፣ የተዛባ ወይም ጤነኛ ያልሆነ አካላዊ ወይም አዕምሮአዊ ሁኔታ ወይም ተያያዥ ምልክቶችን ለመመርመር፣ ለማከም፣ ለማስታገስ ወይም ለመከላከል የሚውል ማንኛውም ንጥረ-ነገር ወይም የንጥረ- ነገሮች ውህድ ሆኖ ባዮሎጂካል መድኃኒት፣ ማከሚያ ምግብ፣ የጤና ቴክኖሎጂ፣ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልግ ሌላ ማንኛውንም የሕክምና መሳሪያ እና የሕክምና መገልገያ ያጠቃልላል፤
- “የቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት” ማለት በበጀት በተደገፈና የመድኃኒት ፍላጎት ላይ በተመሠረተ መንገድ ጤና ተቋማት በቅድሚያ ከአገልግሎቱ ጋር በሚፈፅሙት ውል መሠረት የሚስተናገዱበት የአቅርቦትሥርዓት ነው፤
- “የቅድሚያ ክፍያ” ማለት ውል ለተገባበት መሠረታዊ መድኃኒት የውል ስምምነቱ ላይ በተመለከተው መጣኔ መሰረት አቅርቦት ከመፈጸሙ በፊት በጤና ተቋም ወይም በሚመለከተው አስተዳደር የሚከፈል ገንዘብ ነው፤
- “መሠረታዊ መድኃኒት” ማለት በዋነኛነት የህብረተሰብ ጤናን ከመጠበቅ አኳያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እና በማንኛውም ጊዜ ከክምችት መጥፋት የሌለባቸውን መድኃኒቶች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ በሚኒስቴሩ በሚዘጋጅ የመድኃኒት ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ማንኛውም መድኃኒት ነው፤
- ”ባለድርሻ አካል” ማለት ሚኒስቴሩን፤ የገንዘብ ሚኒስቴርን፤ የክልል ጤና ቢሮን፣ የዞን ጤና መምሪያን፣ ፤የከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ፣ የወረዳ ጤና ጽህፈት ቤትን፣ የጤና ተቋምን፣ የክልል፣የዞንና የወረዳ ፋይናንስ ቢሮን፣ የልማት አጋርን፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን፤ ባንኮችን እና ይሄንን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የሚመለከታቸውን አካላት ያካትታል፡፡
12. በአዋጁ ላይ ትርጉም የተሰጣቸው ቃላትና ሐረጎች በዚህም መመሪያ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
3. የተፈጻሚነት ወሰን
ይህ መመሪያ የቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፤
ክፍል ሁለት
ስለ ቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት
4. የቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት አፈጻጸም
- ማንኛውም የጤና ተቋም በቅድሚያ ውል በተገባለት የአቅርቦት ስርአት ውስጥ በተካተተው የመድኃኒት ፍላጎት ዝርዝር መሰረት ብቻ ይሆናል፤
- የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጸጽ 1 ድንጋጌ ቢኖርም በቅድሚያ ውል በተገባለት ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተ መድኃኒት በጤና ተቋማት ተፈላጊ ሆነው ሲገኙ በአገልግሎቱ ጋር በሚደረግ ስምምነት ሊስተናገዱ ይችላሉ፡፡
- በዚህ አንቀጽ መሠረት አገልግሎቱ የቅድሚያ ውል የሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓትን ተከትሎ ጤና ተቋማት በቅድሚያ እንዲከፍሉ በማድረግ ወይም የእጅ በእጅ ሽያጭ ወይም በብድር ስምምነት መሠረት በዱቤ መድኃኒቶችን ለጤና ተቋማት ያቀርባል፡፡
5. ጤና ተቋማት በቅድሚያ እየከፈሉ የሚስተናገዱበት ሁኔታ
- ዝርዝር አፈጻጸሙ በአገልግሎቱ እና በጤና ተቋማቱ መካከል በሚፈጸመው የቅድሚያ ውል የሚወሰን ሆኖ አገልግሎቱ ጤና ተቋማት የቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ በማድረግ በሚያቀርቡት በበጀት የተደገፈ የመሠረታዊ መድኃኒቶች ፍላጎት ዝርዝር መሠረት ያቀርባል፤
- ቅድሚያ ክፍያ ለሚከፍሉ ጤና ተቋማት አገልግሎቱ የማበረታቻ ስርአት ይዘረጋል፤
- ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 አፈጻጸም ጤና ተቋማት ለመድኃኒት መግዣ ያስያዙት በጀት በቅድሚያ ወደ አገልግሎቱ የሂሳብ ቋት እንዲገባ በማድረግ በቀረበላቸው መሠረታዊ መድኃኒት ልክ ሂሳቡ የሚወራረድበትን አሠራር ስርአት እንዲዘረጋ አገልግሎቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወይም ከሚመለከተው የክልል ፋይናንስ ቢሮ ጋር በትበብበር ይሰራል፡፡
- ጤና ተቋማት የእጅ በእጅ ሽያጭ የሚስተናገዱበት ሁኔታ
የቅድሚያ ውል በተገባለት ስምምነት ዝርዝር ውስጥ ባሉት መድኃኒት ጤና ተቋማት የእጅ በእጅ ሽያጭ ሊከፍሉ ይችላሉ፡፡
7. ጤና ተቋማት በዱቤ የሚስተናገዱበት ሁኔታ
- ዝርዝር አፈጻጸሙ በአገልግሎቱ እና በጤና ተቋማቱ መካከል በሚፈጸመው የቅድሚያ ውል የብድር ስምምነት የሚወሰን ሆኖ በአዋጅ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 14 እና አንቀጽ 23 መሠረት ጤና ተቋማት የሚያቀርቡት በበጀት የተደገፈ የመሠረታዊ መድኃኒቶች ፍላጎትን ተክትሎ አገልግሎቱ መሠረታዊ መድኃኒቶችን በዱቤ ሊያቀርብ ይችላል፤
2) ለዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 አፈጻጸም አገልግሎቱ እንደአግባብነቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር ወይም ከክልል ፋይናንስ ቢሮዎች ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሠረት ለጤና ተቋማቱ መሠረታዊ መድኃኒቶችን በዱቤ ካቀረበ በኋላ አስፈላጊ የሆኑ የሰነድ ማስረጃዎችን ለገንዘብ ሚኒስቴር ወይም ለክልል ፋይናንስ ቢሮዎች በማቅረብ የጤና ተቋማቱ ዕዳ ክፍያ በቀጥታ ወደ አገልግሎቱ የሂሳብ ቋት የሚተላለፍበትንና ሂሳቡ የሚወራረድበትን የአሠራር ስርአት እንዲዘረጋ በትብብር ይሰራል፡፡
ክፍል ሶስት
ተግባርና ኃላፊነት
8. አገልግሎቱ ተግባርና ኃላፊነት
አገልግሎቱ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖሩታል፡-
- በቅድሚያ የውል ስምምነት የሚቀርቡ የመድኃኒት ዝርዝር በማዘጋጀት ለጤና አስተዳደር እና ለጤና ተቋም የማሳወቅ፤
- የቅድሚያ የውል ስምምነት ለሚቀርቡ መድኃኒቶች ግምታዊ የዋጋ ዝርዝር በማዘጋጀት ለጤና ተቋማት ተደራሽ የማድረግ፤
- ጤና ተቋማት በየዓመቱ ለሚያቀርቡት በበጀት የተደገፈ የመድኃኒት ፍላጎት ዝርዝር ከጤና ተቋሙ ጋር ወይም አግባብነት ካለው ጤና አስተዳደር አካል ጋር ውል የመግባት፤
- አመታዊ የጤና ተቋምን የመድኃኒት ፍላጎት በተገባው ውል መሰረት የማደራጀት፤
- ጥራታቸው፣ ደህንነታቸው እና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መሠረታዊ መድኃኒቶችን በተገባው ውል መሰረት የማቅረብ፤
- ጤና ተቋማት በሚያቀርቡት የአቅርቦት ፍላጎት ዕቅድ የጊዜ ሰሌዳ ዝርዝር በደረሰው በውሉ ላይ በሚቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መድኃኒት ለጤና ተቋም የማቅረብ፤
- SÉኃ’>ƒ ŸSLŸ< uòƒ u¨<K< uT>ÑKç¨< S×’@ Sc[ƒ ŸÖpLL ÓUታ© ªÒ ÚUa Ÿ}Ñ– Ö?“}sS< M¿’~” ”Ç=ŸõM ¨ÃU ¾õLÔƒ SÖ’<” ”Ç=Áe}Ÿ¡M ¾Td¨p::
- ከጤና ተቋማት ወይም ከጤና አስተዳደር ጋር በሚገባው የውል ስምምነት መሰረት መድኃኒቶችን ጤና ተቋማት ድረስ የማድረስ፤
- ጤና ተቋማት በገቡት ውል መሰረት ግብዓት መውሰዳቸውን መከታተል እና አፈጻጸሙን በየሩብ ዓመቱ መገምገም፤ ለሚመለከተው የጤና አስተዳደር የማሳወቅ፤
- በቅድሚያ ውል ስምምነቱ ላይ በሚገለጸው መሰረት በጤና ተቋማት የሚፈለጉ መድኃኒቶች በአገልግሎቱ ማቅረብ የማይቻልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ተገቢውን የመፍትሔ አማራጭ ይሰጣል፤
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 10 የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ጤና ተቋም የቅድሚያ ክፍያ የፈጸመ ከሆነ አገልግሎቱ በውሉ መሰረት መድኃኒት የማቅረብ ግዴታ አለበት፤
- ለጤና ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት፤ እንዲሁም የቴክኒካል ድጋፍ ስራዎች ላይ መሳተፍ፤
9. የጤና ተቋም ተግባርና ኃላፊነት
ጤና ተቋማት የሚከተሉት ተግባር እና ኃላፊነት ይኖሩታል
- ጤና ተቋሙ የአከባቢውን የበሽታ ስርጭትና የአገርቱን የመሰረታዊ መድኃኒቶችን ዝርዝር መሰረት በማድረግ በጤና ተቋሙ ቅድሚያ የሚሰጣቸዉን የመድኃኒት ዝርዝር ያዘጋጃል፤ ያጸድቃል፤
- በበጀት የተደገፈ ዓመታዊ ፍላጎትን በማዘጋጀት በጤና ተቋሙ ስራ አመራር ያጸድቃል፤ በጤና ተቋሙ የበላይ ሃላፊ ተፈርሞ ለአገልግሎቱና ለሚመለከተዉ ጤና አስተዳዳር በየዓመቱ እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ድረስ ይልካል፤
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ለለየው የግዥ ፍላጎት ማስፈጸሚያ የሚሆን በቂ በጀት እንዲመደብ የማድረግ፤
- አገልግሎቱ የቅድመ ውል የሚገባበት የመድኃኒት ዝርዝር ባሳወቀው መሰረት የቅድሚያ ውል ከአገልግሎቱ ጋር ይፈራረማል ወይም በሚመለከተው ጤና አስተዳደር እንዲፈረም ያደርጋል፤
- የቅድሚያ ውል ለሚገባበት የአቅርቦት ፍላጎት ዕቅድ የጊዜ ሰሌዳ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት እስከ ሐምሌ 15፣ ሁለተኛው ሩብ ዓመት እስከ ጥቅምት 15፣ ሶስተኛው ሩብ ዓመት እስከ ጥር 15 እና አራተኛው ሩብ ዓመት እስከ ሚያዚያ 30 ለአገልግሎቱ ማቅረብ አለበት፤
- የጠየቃቸውን መድኃኒት ፍላጎት ዝርዝር መጠን የመውሰድ ግዴታ፤
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 6 እንደተጠበቀ ሆኖ ጤና ተቋሙ መድኃኒት ከመረከቡ በፊት በውሉ የሚገለጸው መጣኔ መሰረት ከጠቅላላ ግምታዊ ዋጋ ጨምሮ ከተገኘ ልዩነትን የመክፈል ወይም የፍላጎት መጠኑን የማስተካከል፤
- በውል ስምምነቱ ላይ በተመለከተው የግዥ እቅድ መሰረት መድኃኒቶችን የመረከብ፤
- በውሉ መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ በወቅቱ የሚጠበቅበትን ክፍያ የመፈጻም፤
- የቅድሚያ ውል የተገባበት የአቅርቦት ሥርዓት አፈጻጸምን በየሩብ አመቱ ለጤና አስተዳደር አካላት የማሳወቅ፡፡
ክፍል አራት
ክትትል እና ግምገማ
10. ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያ
- አገልግሎቱ የቅድሚያ ውል የተገባበት የአቅርቦት ሥርዓትን ውጤታማነት ለመገምገም የሚያስችሉ የአፈጻጸም መለኪያዎችን ይቀርጻል፤
- የቅድሚያ ውል የተገባበት የአቅርቦት ሥርዓት ውጤታማነት በአገልግሎቱ የዕቅድ ክትትል እና ግምገማ ማዕቀፍ ውስጥ ተካቶ በየሩብ ዓመቱ እየተገመገመ በግምገማ ውጤቱ ላይ የተመሠረቱ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፤
- ሚኒስቴሩና አገልግሎቱ በጋራ የሚመለከታቸውን የባለድርሻ አካላት ያካተተ የግምገማ ቋሚ ኮሚቴ በማቋቋም የስራውን ተግባራዊነት ይከታተላል፤ ይገመግማል፡፡
ክፍል አምስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
- የቅድሚያ ውል ስለሚፈረምበት ሁኔታ
- የቅድሚያ ውል በሚገባበት የአቅርቦት ሥርዓት በጤና አስተዳደር ወይም በጤና ተቋማት ደረጃ ሊፈረም ይችላል፤
- የቅድሚያ ውል የተገባበት የአቅርቦት ሥርዓት የውል ፊርማ የሚፈጸመው ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 30 ድረስ ይሆናል፡፡
12. የተሻሩና ተፈጻሚ የማይሆኑ ህጎች
ይህንን መመሪያ የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ ወይም የአሰራር ልምድ በዚህ መመሪያ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
13. የመመሪያው ተፈጻሚነት
ይህ መመሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር ተመዝግቦ በአገልግሎት በድረ-ገጽ ላይ ከተጫነበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ግንቦት 2017
አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር