አገልግሎቱ ከአለም አቀፍ መድኃኒት አምራቾች በኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር ተወያዩ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በግሎባል ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ የኤች. አይ. ቪ፣ የቲቢ፣ የወባ መድኃኒቶች እና መመርመሪያ ኪቶች ከሚያቀርቡ አለም አቀፍ አምራቾች በኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር ታህሳስ 11 /2016 ዓ.ም ተወያይተዋል ፡፡
አምራቾቹ ግብዓቶች ወደብ ላይ እንዳይቆዩ የተደራጀ ሰነድ ለአገልግሎቱ በፍጥነት በመላክ እንዲሁም የእርስ በእርስ ተግባቦትን በማሳደግ ፈጣን የህክምና ግብዓቶች አቅርቦት እንዲኖር ማስቻል ይገባቸዋል ሲሉ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ አሣስበዋል፡፡
አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ከውጪ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተገናኘ የተወሰነ የግዢ መዘግየት ምክንያት የክምችት ስጋት እንደነበረበት የአገልግሎቱ የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች ግዥ አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ ተናግረዋል፡፡
አክለውም አሁን ላይ የውጪ ምንዛሬ እጥረት በመቀረፉ የተከናወኑ ግዢዎች በቶሎ ሀገር ውስጥ ገብተው ያለውን ስጋት ለመቅረፍ እና ግሎባል ፈንድ በሶስት አመት አንዴ ለአገልግሎቱ የሚያፀድቀው በጀት የመጨረሻ አመት የቆይታ ጊዜ ላይ በመሆኑ የተመደበውን በጀት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መጠቀም እንደምንችል ማረጋገጥ እና ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ፡፡
በውይይቱ የህንድ፣ የቻይና፣ የአውሮፓ ሀገራት አምራች ተወካዮች እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አስመጪዎች ማህበር የተሳተፉ ሲሆን፤ በቀጣይም በዘላቂነት በየሩብ አመቱ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት አንደሚገማገሙ አቶ ሰለሞን ንጉሴ አመላክተው፤ አሁን ላይ የአጭር ጊዜ እቅዳችን ከውጪ የሚመጡ ግብዓቶችን በማጠናከር ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ አምራቾችን እየደገፍን በመሄድ በረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ እራሷ የህክምና ግብአቶች እንድታመርት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
#ማገልገል ክብር ነው
ሰላም ይደግ
