ስራን በማፋጠን በተሻለ ቅልጥፍና ለህዝቡ የሚፈልገውን መድኃኒት ማቅረብ አለብን

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም ሥራን በማፋጠን በተሻለ ቅልጥፍና ህዝቡ የሚፈልገውን መድኃኒት ማቅረብ አለብን ሲሉ ተናገሩ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ለ3 ወር ያህል ከኤጀንሲው በተመረጡ 25 ሙያተኞች የተጠናው መሠረታዊ የሥራ ሂደት ልወጣ /Business Process transformation or optimization/ ጥናት ማጠቃለያ ሚያዝያ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ እምቢልታ ሆቴል የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል፡፡
አንዳንድ የምንሠራቸው ተግባራት ከወረቀት ቅብብሎሽ ያለፈ አስፈላጊ ሆነው አልተገኙም፡፡ እነዚህን ተግባራት እንዴት እናስወግዳቸው ወይም እናመጋግባቸው፣ ይህን ካደረግን በኋላ ሌላው አለም እንደሚሠራው ኤሌክትሮኒክስ በማድረግ አውቶሜት እናደርጋቸዋለን የሚለው የጥናቱ ክፍል እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ስንታገዝ ሥራችንን ከ45-46% ያሣጥረዋል፡፡ ይህም አሉ ለሠራተኞች እረፍት ለመስጠት ሳይሆን ህዝቡ የፈለገውን መድኃኒት እንዴት በፍጥነት ማድረስ ይቻላል ለሚለው መልስ ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሎኮ ከህዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ሥራችን ሲያጥር ግዢያችን ይቀላጠፋል፡ የመድኃኒት ስርጭቱም ይፈጥናል።
በመሆኑም ለሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ቶሎ ቶሎ እንደርሳለን፡፡ ህብረተሰቡም በተሻለ ዋጋ መድኃኒት ያገኛል ብለዋል፡፡
ቀጣዩ ሥራችን ጥናቱን ወደ ተግባር ማውረድ ነው ያሉት ዶ/ር ሎኮ የሥራ ሂደቶች ሙሉ በሙሉ ተቀርጸዋል፡፡
የተቀረጹትን የሥራ ሂደቶች ካለን አደረጃጀት ጋር በማናበብ እና አንድ ወይም ሁለት የሥራ ሂደት መርጠን የትግበራ ሙከራ በማድረግ ትምህርት ወስደን ሌሎቹ ላይ እንተገብረዋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሙከራውን ለመተግበር ትልቅ የሶፍት ዌር (Software) ግዢ እስኪገዛ አንጠብቅም አሁን ባለን አሠራር እንጀምራለን ብለዋል፡፡ ጥናቱን ካጠኑት ሙያተኞች ተመርጠው ይህንን ሥራ እስከ ሙሉ አውቶሜሽን የሚከታተሉ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡