ኤጀንሲው ለጤና ጣቢያዎች የቀጥታ የመደበኛ መድኃኒት ስርጭት ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው በ3 ቅርንጫፎች ስር ለሚገኙ የተመረጡ 251 ጤና ጣቢያዎች የቀጥታ የመደበኛ መድኃኒት ስርጭት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የመደበኛ መድኃኒቶች የክምችት አስተዳደር ባለሙያ ወ/ት ስምረት የማነ ዛሬ ህዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ገለፁ፡፡
ባለሙያዋ ኤጀንሲው ከጤና ሚኒስቴር ጋር ውይይት ማካሄዱን አስታውቀው ስርጭት የሚካሄድባቸው ቅርንጫፎችም ባህርዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ወ/ት ስምረት በባህርዳር ቅርንጫፍ 374 ጤና ጣቢያዎች፣ በደሴ ቅርንጫፍ 318 እንዲሁም በጎንደር ቅርንጫፍ 158 ጤና ጣቢያዎች ተመርጠዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ኤጀንሲው መድኃኒቶችን ቀጥታ ወደ ጤና ተቋማት ማሠራጨቱ በጤና ተቋማቱ ያልተቆራረጠ የመደበኛ መድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር እንደሚያስችልና ኤጀንሲውን ለክትትልና የገንዘብ አሠባሠቡን የተፋጠነ እንዲሆን ይረዳዋል ሲሉ ባለሙያዋ ገልፀዋል፡፡
በቀጥታ የመድኃኒት ስርጭቱም የመድኃኒት አቅርቦቱን ቢያንስ 80 ፐርሠርንት ለማድረስ እንደታቀደ ገልፀው በኦሮምያ ክልል በተደረገው የቀጥታ ስርጭት ነጌሌ ቦረና 82%፣ ነቀምት 87% እና አዳማ 85% መድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውል እንደሚፈራረምና በዓመት ሁለት ጊዜ የመድኃኒት ስርጭት እንደሚያካሄድ ወ/ት ስምረት አስረድተዋል፡፡
በጸሎት የማነ